የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ከዩኤስአይዲ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ስኮት ሆክላንደር ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ከዩኤስአይዲ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ስኮት ሆክላንደር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 13/ 2016 (ኢዜአ)፦ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስአይዲ) የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ስኮት ሆክላንደር ከተመራ ልዑክ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ውይይቱ በጥር ወር 2016 ዓ.ም ይፋ የተደረገውና በቆላማ አካባቢዎች የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ለተጽእኖ የማይበገሩ የማድረግ አላማ ያለው ‘Partnership for Lowlands Resilience Activity’ ፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።
ለሶስት ዓመት ለሚተገበረው ፕሮጀክት የሚያስፈልገውን የ3 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሸፈነው ዩኤስአይዲ ነው።
ኢትዮጵያና ዩኤስአይዲ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ምክክር መደረጉን ከመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ፕሮጀክቱ በሶማሌ፣ አፋር፣ ኦሮሚያና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል።