ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልልና አካባቢው በሚቀጥሉት ቀናት መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት ይኖራል - ኢንስቲትዩቱ

ጋምቤላ ፤ ነሐሴ 13/ 2016(ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልልና አካባቢው በሚቀጥሉት ቀናት መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት ሊኖር ስለሚችል ሁሉም ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

በኢንስቲትዩቱ የጋምቤላ ክልል ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ተስፋሁን ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት ከተያዘው ነሐሴ ወር 2016 አጋማሽ ጀምሮ በጋምቤላና ተጎራባች አካባቢዎች ጠንከር ያለ የዝናብ ስርጭት ይኖራል።

በዚሁ በክልሉና አካባቢው በቀጣዮቹ ሁለት ሶስት ሳምንታት ውስጥ የሚኖረው መደበኛና ከመደበኛ ያለፈ የዝናብ ስርጭት ለእርሻ ስራ አመች መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ዘግይተው ለሚዘሩና ረዘም ባለ ጊዜ ለሚደርሱ የሰብል ዓይነቶች የዝናብ ስርጭቱ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

በአንፃሩ በተጎራባች አካባቢዎችና በክልሉ በሚኖረው መደበኛና ከመደበኛ ያለፈ የዝናብ ስርጭት ባሮን ጨምሮ ሌሎች ክልሉን አቋርጠው የሚያልፉ ትላልቅ ወንዞች ሞልተው ስለሚፈሱ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል አስገንዝበዋል።

ስለሆነም በወንዞች አካባቢ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ከወዲሁ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደረጉ እንደሚገባ አቶ ተስፋሁን አሳስበዋል።

በጋምቤላ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር አገልግሎት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር አቶ ሰይፉ ወልዴ በበኩላቸው እንዳሉት የአየር  ትንበያ መረጃን መሰረት በማድረግ ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።


 

አገልግሎቱ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የጎርፍ አዳጋ ምላሽ መጠባበቂያ እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱን ለአብነት አንስተዋል።

በተጨማሪም  የጎርፍ መከላከል ግብር ኃይል በየደረጃው በማቋቋም በወንዞች አካባቢ ለሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የጋምቤላ ክልል ዝቅተኛ መልክዓ ምዕድራዊ አቀማመጥ ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በዓመቱ ባሮን ጨምሮ ሌሎች አራት ትላልቅ ወንዞች ሞልተው በመፍሰስ በሚያስከትሉት ጎርፍ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች እንደሚፈናቀሉ ከአገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም