ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት የስፖርት መሠረተ ልማት ግንባታ ብቻ ሳይሆን ተፎካካሪ ብሔራዊ ቡድን ያስፈልጋታል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት የስፖርት መሠረተ ልማት ግንባታ ብቻ ሳይሆን ተፎካካሪ ብሔራዊ ቡድን ያስፈልጋታል
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 13/ 2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት የስፖርት መሠረተ ልማት ግንባታ ብቻ ሳይሆን ተፎካካሪ ብሔራዊ ቡድን ያስፈልጋታል ሲሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ገለፁ።
እ.አ.አ የካቲት 8 ቀን 1957 በአፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ ታሪካዊ ከሚባሉ ቀናት አንዱ ነው።
በዕለቱ በካርቱም ግራንድ ሆቴል ሱዳን፣ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ደቡብ አፍሪካ የአፍሪካን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራውን ተቋም መሠረቱ።
በዚህ መልክ የተጀመረው የአፍሪካ ዋንጫ የተለያዩ ሀገራት እያስተናገዱት ዛሬ ላይ የደረሰ ሲሆን ከመሥራች ሀገሮች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያም ሦስት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን አዘጋጅታለች።
እ.አ.አ በ1962 ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ፤ እ.አ.አ በ1968 ስድስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫና እ.አ.አ በ1976 ደግሞ 10ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ አስተናግዳለች።
ኢትዮጵያ መስራች የሆነችበትንና በ2029 የሚዘጋጀውን የአፍሪካ ዋንጫ በድጋሚ የማዘጋጀት ዕቅድ እንዳላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መግለፃቸው የሚታወስ ነው።
ይህን መነሻ በማድረግ ኢዜአ ያነጋገራቸው የስፖርት ባለሙያዎች የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት የስፖርት መሠረተ ልማት ግንባታ ላይ ብቻ ሳይሆን ተፎካካሪ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት መስራት ያስፈልጋል ሲሉ ገልፀዋል።
የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተርና የፊፋ ቴክኒክ ኤክስፐርት አብርሃም መብራቱ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት በመንግሥት ደረጃ ዕቅድ መያዙ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።
እግር ኳስ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ፋይዳ ያለውን ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የተደረገ መልካም ሀሳብ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካን ዋንጫ ለማዘጋጀት ያላት ጊዜ አጭር በመሆኑ ብሄራዊ ቡድኑን ለማጠናከር ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ለዚህም ደግሞ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብቻ ሳይሆን በስፖርት ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች፣ ባለሀብቶችና መንግሥትም ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋችና አሰልጣኝ ዕድሉ ደረጄ በበኩሉ ኢትዮጵያ ሦስት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ማዘጋጀቷን አስታውሶ አሁንም የማዘጋጀት አቅም አላት ብሏል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የእግር ኳስ ዕውቀት ችግር እንደሌለ በመጥቀስ አሰራሮች ከተስተካከሉ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ማዘጋጀት ትችላለች በማለት ተናግሯል።
የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ሲደረግ ብሔራዊ ቡድኑን ጎን ለጎን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም ተናግሯል።