የትራንስፖርት ዘርፉን በታዳሽ ሃይል ማዘመን የሚያችሉ አሰራሮችና የፖሊሲ ማዕቀፎች እየተዘጋጁ ነው-የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የትራንስፖርት ዘርፉን በታዳሽ ሃይል ማዘመን የሚያችሉ አሰራሮችና የፖሊሲ ማዕቀፎች እየተዘጋጁ ነው-የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 12/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የአየር ትራንስፖርትን ጨምሮ በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በታዳሽ ሃይል ለማዘመን የፖሊሲ ማዕቀፎች እየተዘጋጁ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ኢትዮጵያ የሃይድሮ ኤሌክትሪክን ጨምሮ የነፋስ፣ የእንፋሎት(ጂኦተርማል)፣ የጸሃይ (ሶላር) አማራጮችን ተጠቅማ ከ60ሺ በላይ ሜጋዋት ሃይል የማመንጨት አቅም እንዳላት መረጃዎች ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ የሃይል ፍላጎት ላይ የተደረጉ የዳሰሳ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣በየትኛውም አካባቢ የሃይል ፍላጎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።
ይህን ፍላጎት ለማሟላት ያሉትን የሃይል አማራጮች መጠቀም ወሳኝ መሆኑንም ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚገልጹት።
በተለይም አለምን እየፈተነ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ታዳሽ ሃይልን መጠቀም ለነገ የማይባል መሆኑን በመጥቀስ።
የሊድትኮ ሶላር ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ደረጀ ዋለልኝ እንደሚሉት በኢትዮጵያ በታዳሽ ሃይል ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ውጤታማ እየሆኑ መጥተዋል።
ይሁንና አብዛኞቹ የአገሪቷ አካባቢዎችን በቀላሉ በታዳሽ ሃይል ማስተሳሰርና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ማድረግ ላይ ብዙ መስራት ይጠበቃል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት እያደረገችው ያለውን ጥረት ለማገዝ ታዳሽ ሃይልን መጠቀም ለነገ የማይባል መሆኑንም ነው አቶ ደረጀ የሚያነሱት።
በቅርቡ በኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ሃይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችንም በታዳሽ ሃይል የመተካት ስራ መጀመሩ ለዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይሁንና የታዳሽ ሃይል አጠቃቀም ላይ የህግ ማዕቀፎች አለመኖራቸው በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች በሚፈለገው ልክ እንዳይሰሩ ማድረጉን አንስተዋል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ከፍተኛ አማካሪ ጎሳዬ መንግስቴ (ዶ/ር) እንደሚሉት በኢትዮጵያ ታዳሽ ሃይልን በመጠቀም አረንጓዴ ልማትን ማረጋገጥና የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል በልዩ ትኩረት እየተሰራበት ነው።
አገሪቷ ነዳጅን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያስገባች እንደመሆኑ ይህን ሊተካ የሚችል ታዳሽ ኢነርጂ ላይ በትኩረት መስራቷ ተገቢና ውጤታማ መሆኑንም አንስተዋል።
በዚህ ረገድ የአየር ትራንስፖርትን ጨምሮ በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በታዳሽ ሃይል መተካት የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎችና የአሰራር ስርዓቶች እየተዘረጉ መሆኑንም አብራርተዋል።