የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በፋይናንስ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት አሳድሮብናል- የፋይንቴክ ኩባንያዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በፋይናንስ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት አሳድሮብናል- የፋይንቴክ ኩባንያዎች
አዲስ አበባ ነሐሴ 12፤ 2016(ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በፋይናንስ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት አሳድሮብናል ሲሉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ አቅራቢ ኩባንያዎች (ፋይንቴክ) ገለጹ።
የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ለአካታች የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት ወሳኝ መሆኑንም ኩባንያዎቹ ገልጸዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ መደረጉ ለኢንቨስትመንት ዝግ የነበሩ መስኮች ክፍት እንዲሆኑ ተደርጓል።
ለአብነትም በውጭ ምንዛሬ አስተዳድር የተደረገው ማሻሻያ እንዲሁም የፋይናንስ አገልግሎት ዘርፉ ለውጭ ተቋማት ክፍት እንዲሆን መወሰኑ ባንኰችን ጨምሮ የፋይናንስ ዘርፍ ተዋናዮችን ቀልብ እየሳበ መጥቷል።
በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራችው የፋይናንስ ተቋማት ቴክኖሎጂ አቅራቢና አማካሪ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች፤ ኢትዮጵያ በፖሊሲ ማሻሻያ ላይ የወሰደቸው እርምጃ ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ከእነዚህ መካከል ''ፊናክል ሶሉሺን'' የተሰኘው የሕንዱ ዓለም አቀፍ የባንክ አማካሪ ኩባንያ ሃላፊ ናሬሽ ብሀኖትራ፤ የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለምጣኔ ሃብቷ ዘላቂ እድገት መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።
የዘርፉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችም መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ በር የሚከፍትና ለሀገር በቀልና ለውጭ ፋይናንስ ተቋማት የጋራ ትብብር፣ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
በፋይናንስ ተቋማት ትስስር ላይ የሚሰራው የዓለም ስትራቴጂክ ጥምረት ማዕከል የእስትራቴጂ ትብብር ኃላፊ መሀመድ ቶፊቅ፤ በርካታ ታዳጊ ሀገራት ያደረጉት የፖሊሲ ማሻሻያ ለኢኮኖሚ ዕድገት ምህዋር ሆኗቸዋል ይላሉ።
በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ትግበራ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንስተዋል።
መሰረቱን ደቡብ አፍሪካ ያደረገው የ"ኢ ኤፍ ቲ" ኮርፖሬሽን ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክላይተን ሀይዋርድ፤ ኩባንያው ለዲጂታል ባንክ አገልግሎት የሚበጁ ቴክኖሎጂዎችን የሚያቀርብ መሆኑን አንስተዋል።
ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በኢትዮጵያ እንዲሰማሩ መፈቀዱ ለአካታች ፋይናንስ ስርዓት ትግበራ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ዘመኑን በዋጁ ቴክኖሎጂዎች ታግዘው በኢትዮጵያ እንዲሰማሩ ያደርጋል ብለዋል።
በአብዛኛው የዓለም ሀገራት አገልግሎት የሚሰጠው ኬኒያ በቀሉ የ''ካስፐርስኪ'' ዓለም አቀፍ የዲጂታል ባንክ ቴክኖሎጂ አቅራቢ ኩባንያ ሽያጭ ኀላፊ ቤተል ኦፒል ይህን ሃሳብ ይጋራሉ።
ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላትና ግዙፍ ኢኮኖሚ የምታንቀሳቅሰው ኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ባለድርሻ አካላት ክፍት ማድረጓ ኩባንያዎቹን በመሳብ ዘርፉ አካታችና ተደራሽ እንዲሆን ያስችላል ብለዋል።
'ኪኤምፒጂ'' የተሰኘው ሌላው የባንክ ቴክኖሎጂ አቅራቢ ድርጅት የቴክኖሎጂ ሽግግር ክፍል ዳይሬክተር ማቲን ኪማኒ፤ የአፍሪካ ሀገራት በትስስር እንጂ በተናጠል ዘላቂ ዕድገት ማምጣት የማይችሉ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በፋይናንስ ዘርፍ ያደረገችው ማሻሻያ የዓለም ኩባንያዎችን ቀልብ የሚስብ እና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እምርታም መሰረት የሚጥል መሆኑን ገልጸዋል።
በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ለሚንቀሳቀሱ የፋይናንስ ተቋማት የበለጠ ትስስር እንዲፈጥሩ እና ድንበር ዘለል ተደራሽነት እንዲያሰፉ ያስችላል ሲሉም ተናግረዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ተከትሎ ኩባንያዎቹ በፋይናንስ ኢንቨስትመንት ዘርፎች መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ የዘርፉ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣትም በተለይም ለስራ ዕድል ፈጠራ፣ ለዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር የላቀ አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል።