ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልማት በአካባቢ ጥበቃና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው - የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና ሚኒስትሮች

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 12/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልማት በአከባቢ ጥበቃና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና ሚኒስትሮች ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ነሐሴ 17 በሚካሄደው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 600 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል አሻራችንን እናኑር በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በእለቱ አዋቂዎች ከ20 በላይ፣ ታዳጊወች ደግሞ ከ10 በላይ ችግኞችን በመትከል ለሀገር ያለንን ፍቅር፣ ለትውልድ ያለንን ስጦታ በተገቢው ስፍራ እንግለጥ ብለዋል።


 

በዚሁ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፤ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አዲስ ታሪክ መስራቷን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ዓመትም በሀገር አቀፍ ደረጃ ነሐሴ 17 ቀን ለሚካሄደው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር፤ በክልሉ አስፈላጊው ሁሉ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው በክልሉ ለአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ ስኬት ሁላችንም ተዘጋጅተናል ብለዋል።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፤ በድሬደዋ ከተማ አስተዳዳር በአንድ ጀምበር አንድ ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡


 

በከተማዋ በአራት ክላስተሮችና በዘጠኝ ወረዳዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ነሐሴ 17 ቀን በነቂስ ወጥተው አሻራቸውን እንዲያሳርፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ለነሐሴ 17 የአንድ ጀምበር የችግኝ የተከላ መርሃ ግብር ዜጎች በነቂስ ወጥተው አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡


 

የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በስኬት መቀጠሉን ገልጸዋል።


 

በአካባቢ ጥበቃ፣ በአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ነሐሴ 17 በሚከናወነው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ሁሉም እንዲሳተፍ ጠይቀዋል።

በ2015 ዓ.ም በአንድ ጀምበር ከ566 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም