ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ቡና የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 12/2016 (ኢዜአ)፡-  ኢትዮጵያ ቡና በ2024/25 የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ከኬንያው ኬንያ ፖሊስ ጋር ዛሬ ያከናውናል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ናይሮቢ በሚገኘው ንያዮ ብሔራዊ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።

ኢትዮጵያ ቡና ለጨዋታው 18 ተጫዋቾችና 6 የአሰልጣኝ ቡድን አባላትን በመያዝ ትናንት ናይሮቢ መግባቱን ኢዜአ ከስፖርት ክለቡ ያገኘው መረጃ ያመለክታል። 

ቡናማዎቹ በገቡበት ዕለት ጨዋታው በሚደረግበት ሜዳ ልምምዳቸውን አድርገዋል።

ኢትዮጵያ ቡና የአገር ቤት ዝግጅቱን በአዳማ ማካሄዱ ይታወቃል።

የሁለቱ ክለቦች የመልስ ጨዋታ እሁድ ነሐሴ 19 ቀን 2016 ዓ.ም በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይከናወናል።

ቡናማዎቹ በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፋ በሁለተኛው ዙር ከግብጹ ዛማሌክ ጋር ይጫወታሉ።

ኢትዮጵያ ቡና በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ነው።

በተያያዘም በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ኢትዮጵያን የወከለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ትናንት ከሜዳው ውጪ ባደረገው የመጀመሪያ ዙር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የዩጋንዳውን ቪላ ክለብ 2 ለ 1 ማሸነፉ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም