ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የተከናወነው ዓለም አቀፍ የቦክስ ውድድር ፍፃሜውን አገኘ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 12/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት  የተከናወነው  ዓለም አቀፍ የቦክስ ውድድር   ሌሊቱን  ፍፃሜውን አግኝቷል ።

በውድድሩ ኢትዮጵያውያን ቦክሰኞች ድል ሳይቀናቸው ቀርቷል።

በውድድሩ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢያሱ ወሰን ፣የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

ውድድሩም በ75 ኪሎግራም መካከለኛ ሚዛን የሴቶች ውድድር ሲጀመር ናይጄሪያዊቷ ፓትሬሽያ ማባታና ሞዛምቢካዊቷ ራዲ አደሲንዳ ግጥሚያቸውን አድርገዋል።

በውጤቱም ናይጄሪያዊቷ ፓትሬሽያ ማባታ በ6 ዙር በተደረገ ውድድር በድምር ውጤት አሸናፊ ሆናለች።

በወንዶች የ 60 ኪሎግራም ቀላል ሚዛን ውድድር ኢትዮጵያዊው አቡበከር ሰፋንና ጋናዊው ጆሴፍ ኮሜይ ባደረጉት ግጥሚያ ጆሴፍ ኮሜይ በ6 ዙር ድምር ውጤት አሸናፊ ሆኗል።

በሌላ ውድድር በ75 ኪሎግራም መካከለኛ ሚዛን ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ተመስገን ምትኩ ከሞሮኮው ያሲኔ ኢሎረዝ ጋር ውድድሩን አድርጓል።

በውጤቱም ያሲኔ ኢሎረዝ በ6 ዙር ድምር ውጤት አሸናፊ ሆኗል።

በወንዶች 48 ኪሎግራም ቀላል ሚዛን ሩሲያዊው ኢድመንድ ኩሁዶዮን ከሜክሲኮዊው ዳንኤል ቫላዴራዝ ጋር ውድድራቸውን ያደረጉ ሲሆን ሩሲያዊው ኢድመንድ ኩሁዶዮን በ8 ዙር ድምር ውጤት አሸንፏል።

በተመሳሳይ በወንዶች 48 ኪሎግራም ቀላል ሚዛን ውድድር ኡዝቤኪስታናዊው ኖዲርጆን ሚዝራክሜዶቭ ከካዛኪስታናዊው ቴምራትስ ዝሁስፖቭ ጋር ውድድሩን አድርጓል።

በውጤቱም ካዛኪስታናዊው ቴምራትስ ዝሁስፖቭ በ8 ዙር ድምር ውጤት አሸንፏል።

በወንዶች 51 ኪሎግራም ቀላል ሚዛን ውድድር ደግሞ ጋናዊው አሎቲ ቲዮፊለስ ከዛምቢያዊው ፓትሪክ ችንዬምባ ጋር ውድድራቸውን አድርገዋል።

በውጤቱም ዛምቢያዊው ፓትሪክ ችንዬምባ በ 4 ዙር በተደረገ ውድድር ድምር ውጤት አሸንፏል።

የዕለቱ የውድድሩ መዝጊያ ጨዋታ ደግሞ በወንዶች 80 ኪሎግራም ከባድ ሚዛን ተደርጓል።

በዚህም ታንዛኒያዊው ዩሱፍ ቻንጋላዌና የዲሞክራቲክ ኮንጎው ፒታ ካቤጂ ጨዋታቸውን አድርገዋል።

በውጤቱም ታንዛንያዊው ዮሱፍ ቻንጋላዊ በ8 ዙር በተደረገ ውድድር ድምር ውጤት አሸንፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም