ምክር ቤቱ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮን ለማጠናከር የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮን ለማጠናከር የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
ቡታጅራ ፤ ነሐሴ 11/2016(ኢዜአ)፦ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የነዳጅ ማደያዎች ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮን ለማጠናከር እንዲያግዝ ከ7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸምን የሚገመግምና ቀጣይ አቅጣጮች ላይ የመከረ መድረክ በቡታጅራ ከተማ አካሂዷል።
የምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ወንድወሰን አርጋው ከ7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ለቢሮው ስራ የሚያግዙ ቁሶችን ለክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስረክበዋል።
እርሳቸው በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ክልሉ ከተመሰረተበት ማግስት ጀምሮ ዘላቂ ሰላምን በማጠናከር፣ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ተጨባጭ ውጤቶች እየታዩ ነው።
እንዲሁም በግብር ከፋዩ ማህበረሰብና ግብር ሰብሳቢው መካከል የነበሩ ክፍተቶችን በመድፈን የተረጋጋ የንግድ ስርዓት እንዲኖር እየተሰራ ያለው ስራ አበረታች መሆኑንም ተናግርዋል።
በተለይም በህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ምክንያት ህጋዊ ነጋዴዎች ለጉዳት እንዳይዳረጉና ኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረውን ተዕጽኖ ለመከላከል የሚደረጉ ጥረቶች ሊጠናከሩ ይገባል ብለዋል።
በዚህም በተለይም የንግዱን ማህበረሰብን ጭምር በማሳተፍና በመቀራረብ እየተደረጉ ያሉ ተግባራት የባለቤትነት ስሜትን ይበልጥ እያዳበሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ስራውን ለማጠናከር ማህበሩ የሚያደርገውን ጥረት አጠናሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ምክር ቤቱ በክልሉ የሚገኙ 81 የነዳጅ ማደያ ባለቤቶችን ማካተቱን ያነሱት አቶ ወንድወሰን፣ ምክር ቤቱ የነዳጅ አቅርቦት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በተቀናጀ መንገድ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ምክር ቤቱ ከክልሉ የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በዛሬው እለትም ከ7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
በዚህም 18 ዴስክ ቶፕ ኮምፒውተሮች እና 16 ላፕቶፖች ድጋፍ መደረጉን ጠቁመው፣ ድጋፉ ቢሮውን ለማጠናከር እየተደረገ ላለው እንቅስቃሴ አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው በበኩላቸው ማህበሩ ከቢሮው ጋር በተቀናጀና በተናበበ መልኩ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለት ያደረገው የቁሳቁስ ድጋፍ የቢሮ ሥራዎችን ለማቀላጠፍ የሚያግዝ በመሆኑን ማህበሩን አመስግነዋል።
ቢሮው አሳታፊ በሆነ መልኩ ፍትሃዊ የንግድ ስርዓት እንዲሰፍን በሚያደርገው ጠንካራ ሥራ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑንም አቶ ዳንኤል ጠቁመዋል።
ይህ እንዲጠናከር በተለይ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ሁሉም የሚያደርገውን ጥረት ማጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በተገኙበት በእዚህ መድረክ ቢሮው የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አካላት የዕውቅና ምስክር ወረቀት እና ሌሎች ሽልማቶችን ሰጥቷል።