የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚያበረታታ ተገማች የቢዝነስ ከባቢ ይፈጥራል - ኢዜአ አማርኛ
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚያበረታታ ተገማች የቢዝነስ ከባቢ ይፈጥራል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2016(ኢዜአ)፦ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚያበረታታ ፣የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚና ተገማች የቢዝነስ ከባቢ እንደሚፈጥር የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገለጹ።
በአይሻ አንድ የነፋስ ኃይል ማመንጫ በ620 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር 300 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ሥምምነት ተፈርሟል።
የትግበራ ሥምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴና የአሚአ ፖወር ሊቀ-መንበር ሁሴን አል ኖዋይስ ተፈራርመዋል።
በተመሳሳይ አሚአ ፓወር በአይሻ አንድ የነፋስ ኃይል ማመንጫ የሚያመነጨውን ኃይል ለኢትዮጵያ ለመሸጥ የኩባንያው ሊቀ-መንበር ሁሴን አል ኖዋይስና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ተፈራርመዋል።
ተቀማጭነቱን በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ያደረገ በታዳሽ ኃይል ልማት፣ ግንባታና አስተዳደር ዘርፍ የተሰማራው አሚአ ፓወር በአይሻ አንድ የነፋስ ኃይል ማመንጫ 300 ሜጋ ዋት በማመንጨት ለ25 ዓመታት ለኢትዮጵያ ለመሸጭ ነው ሥምምነቱን የፈጸመው።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ20 በላይ የዓለም አገራት በታዳሽ ኃይል ዘርፍ የተሰማራው አሚአ ፓወር፣ በአይሻ አንድ የነፋስ ኃይል ማመንጫን ሙሉ በሙሉ በራሱ በመገንባት ያመነጨውን ለኢትዮጵያ እንደሚሸጥ ነው በመድረኩ የተገለጸው።
ፕሮጀክቱ ከአራት ሚሊየን በላይ ቤተሰብ የኃይል ተጠቃሚ ከማድረግም ባለፈ በዓመት ከ690 ሺህ ቶን በላይ የበካይ ጋዝ ልቀትን ይቀንሳል ተብሏል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የሚሰማሩ ኩባንያዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ፍላጎታቸው እያደገ መጥቷል።
ለዚህም በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቅርቡ ገቢራዊ ያደረገችው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ ለሚፈልጉ የውጭ ባለሃብቶች ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።
የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸው ከአሚአ ፓወር ጋር የተደረገው ሥምምነት ትብብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማሳያ ነው ብለዋል።
የአይሻ አንድ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአፍሪካ የአረንጓዴ ኃይል ሽግግር በመፍጠር ቀጣይነት ያለው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ማሳያ ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ የማኅበረሰብ ልማትን በማቀላጠፍ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፉን በማሳደግና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በመፍጠር ለአገር ውስጥና ለቀጣናው ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ነው ያሉት።
የአሚአ ፓወር ሊቀ-መንበር ሁሴን አል ኖዋይስ፣ ፕሮጀክቱን ገቢራዊ ለማድረግ ከአካባቢው ማኅበረሰብና መንግሥት ጋር ለመሥራት ቁርጠኛ ነን ብለዋል።
የአይሻ አንድ የነፋስ ኃይል ማመንጫ በአፍሪካ ቀንድ ግዙፉ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከኢትዮጵያ ጋር እንደዚህ አይነት ሥምምነት መፈራረማችን ልዩ ያደርገዋል ነው ያሉት።