ቀጥታ፡

ተሽከርካሪዎች ከተፈቀደ ክብደት በላይ በመጫን በመንገድ ኃብት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ ቅንጅታዊ ሥራ ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2016(ኢዜአ)፦ ተሽከርካሪዎች ከተፈቀደ ክብደት በላይ በመጫን በመንገድ ኃብት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ ቅንጅታዊ ሥራ ማጠናከር እንደሚገባ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።     

በተሽከርካሪዎች ክብደት ቁጥጥርና ከከብደት በላይ በመጫን በመንገድ ኃብት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሩያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።


 

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ መንግሥት ባለፉት ዓመታት ለመንገድ መሠረተ ልማት በየዓመቱ ከ70 ቢሊየን ብር በላይ ፈሰስ እያደረገ ነው።

ባለፈው በጀት ዓመት ለጂቡቲ ኮሪደር ብቻ የመንገድ ጥገና ከ550 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ከፍተኛ የአገር የኃብት ወጥቶበት የተገነባውን መንገድ ከጉዳት ለመጠቅ ሁሉም ባለድርሻ  አካላት በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በቀጣይ ሁሉንም የሚዛን መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች አውቶሜት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የተሽከርካሪዎች መጠንና ክብደትን ለመወሰንና ለመቆጣጠር ደንብ ቁጥር 491/2014 ወጥቶ በሥራ ላይ ይገኛል።

ከተፈቀደ በላይ ክብደት ጭነት ምክንያት በመንገድ መሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ የሚገኙ ተሽከርካሪዎችን ክብደት ለመቆጣጠር የሚዛን ጣቢያዎች በተለያዩ አካባቢዎች በሥራ ላይ ይገኛሉ።

በመሆኑም ተሽከርካሪዎች በሕግ የተፈቀደላቸውን ክብደት በተመለከተ የወጣውን የጭነት ደንብ በመንገዶች ላይ የማስከበር ኃላፊነት ከሁሉም የሚጠበቅ መሆኑም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የመንገድ ኃብት ማኔጅመንት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር አለማየሁ አየለ (ዶ/ር) በበኩላቸው ተሽከርካሪዎች ከክብደት በላይ በመጫን በመንገድ ላይ ጉዳት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው። 


 

በመንገድ ላይ በሚያደርሱት ጉዳት የተነሳ ለመንገድ ጥገና የሚወጣ ወጪ በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው ለአብነትም በ2016 በጀት ዓመት ለመንገድ ጥገና 8 ቢሊየን ብር ተመድቦ እንደተሰራበት ተናግረዋል።

የውይይቱ የተሳተፊዎች በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ባሉት የተሽከርካሪዎች ክብደት መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ወጥነት ያለው አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሚዛን ጣቢያዎች ተሽከርካሪዎች በፍጥነት የሚስተናገዱበት አሰራር መዘርጋት እንደሚገባና ተቀራርቦ መሥራት እንደሚያስፈልግ ሃሳብ ሰጥተዋል። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም