ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ውድድርን በድል ጀምሯል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ውድድር የሩዋንዳውን ራዮን ስፖርት 3 ለ 2 አሸንፏል።

ውድድሩ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተጀምሯል።


 

ኢትዮጵያን ወክሎ በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሚወዳደረው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሩዋንዳውን ራዮን ስፖርት 3 ለ 2 ረቷል።

አጥቂዋ አረጋሽ ካልሳ ሁለት ግቦችን ስታስቆጠር ሌላኛዋ የፊት መስመር ተሰላፊ ሴናፍ ዋቁማ ቀሪዋን ግብ ከመረብ ጋር አገናኝታለች።

ጂኒን ሙካንዳይሴንጋና ጂያኔት አኩዌንኩንዳ ለራዮን ግቦቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነትና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትና የሴካፋ ምክትል ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጅራ በውድድሩ መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ታድመዋል።


 

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለተኛ ጨዋታውን ማክሰኞ ነሐሴ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ከደቡብ ሱዳኑ ዬ ጆይንት ስታርስ ጋር ያደርጋል።

ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በምድብ 1 ከኬንያው ኬንያ ፖሊስ ቡሌትስ፣ ከሩዋንዳው ራዮን ስፖርትስ፣ ከደቡብ ሱዳኑ ዬ ጆይንት ስታርስና ከዛንዚባሩ ዋሪየር ኩዊንስ ጋር ተደልድሏል።

የታንዛኒያው ሲምባ ኩዊንስ፣ የብሩንዲው ፒቪፒ ቡዬንዚ፣ የዩጋንዳው ካዌምፔ ሙስሊምና የጅቡቲው ፋድ በምድብ 2 የተደለደሉ ክለቦች ናቸው።

መርሐ ግብሩ ነገም ቀጥሎ ሲውል በምድብ 1 ኬንያ ፖሊስ ቡሌትስ ከደቡብ ሱዳኑ ዬ ጆይንት ስታርስ ጋር ከቀኑ 9 ሰዓት በአበበ በቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የሴካፋ ዞን ማጣሪያ እስከ ነሐሴ 26 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።

ውድድሩን የሚያሸንፈው ክለብ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዞን ወክሎ በ2024/25 የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ይሳተፋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም