ቀጥታ፡

በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ላይ እየተሰጠን ያለው ሥልጠና በዘርፉ ያለንን እውቀት ለማዳበር አግዞናል - ሠልጣኝ ታዳጊዎች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በሰው ሰራሽ አስተውሎት እየሰጠ ያለው ሥልጠና በዘርፉ ያላቸውን እውቀት ለማዳበር እድል እንደፈጠረላቸው ሠልጣኝ ታዳጊዎች ገለፁ። 

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የዘንድሮውን የታዳጊዎች የክረምት ሥልጠና (Summer Camp 2024) በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለታዳጊዎች ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢንስቲትዩቲ ሠልጣኞች፤ ኢንስቲትዩቱ በሰው ሰራሽ አስተውሎት እየሰጠ ያለው ሥልጠና በዘርፉ ያላቸውን እውቀት ለማዳበር እድል እንደፈጠረላቸው ጠቁመዋል።

ከሠልጣኞቹ መካከል የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው በእምነት ግሩም በሥልጠናው ሮቦት እንዴት መሥራት እንደሚቻልና ኮድ ማድረግ የሚያስችል እውቀት እያገኘች መሆኑን ገልፃለች።

በሥልጠናው ከምታገኘው እውቀትና ክህሎት የግብርናውን ዘርፍ የሚያግዝ ሮቦት በመሥራት የአገሪቱን የግብርና ዘርፍ ለማዘመን ሕልም እንዳላት ተናግራለች።

ሌላኛው የ11 ኛ ክፍል ተማሪ አዶንያስ ጋርዳቸው፤ በሥልጠናው በሰው ሰራሽ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለውን አቅም ለማሳደግ የሚያስችል እውቅት እያገኘሁ ነው ብሏል።  

በሥልጠናው በሚያገኘው እውቀት የአገሪቱ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነውን ግብርና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ለማዘመን ህልም እንዳለው ነው የገለጸው። 

የ12 ክፍል ተማሪ የሆነችው ቃልኪዳን ስጦታው በበኩሏ ሥልጠናው በንድፈ ኃሳብና በተግባር ልምምድ እየወሰደች መሆኗን ተናግራለች።

ይህም በሰው ሰራሽ አስተውሎት ያላትን እውቀት የበለጠ ለማዳበር እንደሚያስችላት ጠቁማለች።


 

በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የኢንዱስትሪያልና ሮቦትክስ አውቶሜሽን ክፍል ባለሙያና አሰልጣኝ ኢንጂነር ደረጀ ብርሃኑ ሥልጠናው ለሁለት ወራት የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

ሥልጠና በኤ.አይ ቤዚክስ፣ ሮቦቲክስ፣ ማሽን ለርኒንግና ፕሮግራሚንግ፣ ኣይ.ኦ.ቲና ተያያዥ የሰው ሰራሽ አስተውሎት እውቀትና ክህሎቶች ላይ በማተኮር ሥልጠናው እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።  


 

የኢንስቲትዩቱ የኮሙኑኬሽን ዳይሬክተር ተስፋዬ ዘውዴ፤ ኢንስቲትዩቱ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ በአፍሪካ ቀዳሚ ለመሆን ታዳጊዎች ላይ እየሰራ ነው ብለዋል።`

ለአንደኛና ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በዘርፉ ሥልጠና በማዘጋጀት ትውልዱ ስለ ሰው ሰራሽ አስተውሎት  እውቀት እንዲያዳብሩ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ዘንድሮ ለሦስተኛ ዙር እየተካሄደ ባለው የሰመር ካምፕ ሥልጠና በዘርፉ ዝንባሌ ያላቸው 200 ታዳጊዎች ሥልጠናውን እየወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል። 

ሥልጠናው በሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ ላይ ሙያዊ እውቀትና ክህሎት ያላቸውን የሰው ኃይል በብዛትና በጥራት ለማግኘት እንደሚያግዝ አመላክተዋል። 

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ለወጣቱ ትውልድ ማስተማር ለዲጂታል ኢትዮጵያ እውን መሆን ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም