ቀጥታ፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ23 ሺህ በላይ ምርትና አገልግሎቶች የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2016(ኢዜአ)፦ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ23 ሺህ በላይ ምርትና አገልግሎቶች የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት መሰጠቱን የኢትዮጵያ የተስማሚነትና ምዘና ድርጅት ገለጸ። 

የኢትዮጵያ የተስማሚነትና ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር መዓዛ አበራ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የጥራት መሰረተ-ልማት ተቋማትን ለማጠናከር በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው። 

በዚህም የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት የፍተሻ ላቦራቶሪዎችን የማደራጀት ተግባር በልዩ ትኩረት በመሠራቱ ተቋሙ የተሰጠውን ትልዕኮ በአግባቡ እንዲወጣ ማድረጉን ተናግረዋል።

ይህም ዓለም አቀፍ እውቅናና ተቀባይነት ያለው የተስማሚነት ምዘናና የሥልጠና አገልግሎትን ለአምራቾችና ለአገልግሎት ሰጪዎች፣ ለላኪዎች፣ ለአስመጪዎችና ለተቆጣጣሪ አካላት ለመስጠት ማስቻሉን ተናግረዋል።

ድርጅቱ ባሉት 9 የፍተሻ ላብራቶሪዎች በማደራጀት ምግብ፣ የግብርና ምርቶችና ግብዓቶች፣ ኬሚካሎች፣ ማዕድኖች እንዲሁም ለኮንስትራክሽን ግብዓት የሚሆኑ ቆርቆሮ፣ ብረትና ስሚንቶ፣ ጨርቃጨርቅ፣ የቆዳ ውጤቶችን እንዲሁም ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች የፍተሻ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

የምርት ንድፍ፣ ምርትን፣ አገልግሎትን፣ የሥራ ሂደትን ወይም የሥራ ቦታን ከተቀመጠለት መሥፈርትና ከሙያዊ ምዘና አንፃር ተስማሚነትን የሚያረጋግጥ የኢንስፔክሽን አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመዋል

ድርጅቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ23 ሺህ በላይ የአገልግሎት ጥያቄዎች የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት መስጠቱን ተናግረዋል።

አገልግሎቱ የተሰጠው በምርት ጥራት የፍተሻ ላቦራቶሪ፣ በወጪና ገቢ ምርት ኢንስፔክሽን እንዲሁም በሰርቲፊኬሽን መሆኑን ጠቁመዋል። 

ይህም ከባለፊው አመት ጋር ሲነፃፀር የ 25 በመቶ ብላጫ እንዳለው ዋና ዳይሬክተሯ አመላክተዋል።

በተስማሚነት ምዘና አገልግሎት ውስጥ ማለፍ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የተገልጋይን እርካታ ለማሳደግና የሚያመርቱት ምርት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ድርጅቱ የጥራት ማረጋገጥ ሥራዎችን በማከናወን በማደግ ላይ ያለውን ኢኮኖሚ በአስተማማኝ መሠረት ላይ በመገንባትና ቀጣይነቱን በማረጋገጥ ሃላፊነቱን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም