ቀጥታ፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ጠንካራ የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ ተከናውኗል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2016(ኢዜአ)፦በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ጠንካራ  የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ መከናወኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፈንታ ገለጹ።

ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፈንታ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ማኅበረሰቡን ያቀፈ የወንጀል መከላከል ስትራተጂ ተቀርጾ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንንም በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ የፌዴራል ፖሊስ የሕዝብ ተሳትፎ የእጅ ስልክ መተግበሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል።

በዚህም ማንኛውም ዜጋ ከየትኛውም ቦታ ሆኖ የድምጽ፣ የምስል እንዲሁም የጽሁፍ መልዕክቶችን ለፖሊስ ማሳወቅ ይችላል ብለዋል።

ይህም በተላከው መረጃ ላይ ተመርኩዞ ፈጣን የሆነ ምላሽ የመስጠት አቅም መፍጠሩን አመላክተዋል።

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የኢትዮጵያን አጠቃላይ የጸጥታ ሁኔታ ብቻ አተኩሮ የሚሰራ ወንጀል መከላከል ውጤት እንደማያመጣ ገልጸዋል።

በመሆኑም ዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍና ቀጣናዊ ሁኔታዎችን በመለየት የኢትዮጵያን ሰላም ሊያውኩ የሚችሉ ጉዳዮችን በመለየት መመከት የሚያስችል እቅድ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ በተለይም የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል ከዓለም አቀፍ ተቋማትና አጎራባች አገራት ጋር የጋራ እቅድ በማውጣት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ከድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች መካከል ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ የአደገኛ እጽ ዝውውር፣ ገቢና ወጪ ኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

እነዚህን ለመከላከል ከመከላከያ ሰራዊት፣ ከጉሙሩክ ኮሚሽንና ከክልል ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በከፍተኛ ሁኔታ የመቆጣጠር ሥራው እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን የመከላከል አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት የገቢና ወጪ ኮንትሮባንድ ላይ በተሰራ ሥራ ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ሕገ-ወጥ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል ብለዋል።

ተሽከርካሪዎች፣ የውጭ አገራት ገንዘቦችና ማዕድናት እንዲሁም አደገኛ እፆችን ጨምሮ ከሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ በርካታ ኮብላዮችና አስኮብላዮች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም