ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ዘመናዊ የሰራዊት ግንባታን በቴክኖሎጂ ማገዝ የሚችሉ ብቁ ሙያተኞች እያፈራ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ዘመናዊ የሰራዊት ግንባታን በቴክኖሎጂ ማገዝ የሚችሉ ብቁና ሥነ-ምግባር ያላቸውን ሙያተኞች እያፈራ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትርና የዩኒቨርስቲው የቦርድ ሰብሳቢ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ። 

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በምህንድስና፣ ጤና ሳይንስና በኃብት አስተዳደር የትምህርት መርኃ ግብሮች በመጀመሪያ፣ ሁለተኛ ዲግሪና ዶክትሬት ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።


 

በምረቃ መርኃ ግብሩ የፕላንና ልማት ሚኒስትርና የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የመከላከያ ሚኒስቴር ዴኤታዎች፣ የመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች፣ የተለያዩ አገራት ወታደራዊ አታሼዎችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትርና የዩኒቨርስቲው የቦርድ ሰብሳቢ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ፤ ዩኒቨርስቲው ተልዕኮውን በብቃት ማሳካት የሚያስችለውን የተለያዩ የሪፎርም ተግባራት አከናውኗል ብለዋል።

በዚህም አገርና ሕዝብን የሚያኮሩ በተለያዩ የሙያ መስክ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን እያፈራ መሆኑን ጠቅሰው ዩኒቨርስቲው በተለይም ዘመናዊ የሰራዊት ግንባታን በቴክኖሎጂ ማገዝ የሚችሉ ብቁና ሥነ-ምግባር ያላቸውን ሙያተኞች እያፈራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

እንዲያም ሆኖ ዘመኑ የቴክኖሎጂ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቅ ላይ ይበልጥ ርብርብ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ኮማንዳንት ብርጋዴር ጄኔራል ከበደ ረጋሳ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት መርኃ ግብሮች የሰለጠነ የሰው ኃይል እያፈራ ይገኛል ብለዋል።


 

መርኃ ግብሮቹም ተልዕኮውን በብቃት የሚወጣ ሰራዊት በማፍራት ላይ እንደሚገኝና በጥናትና ምርምር ዘርፍም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማፍለቅ ዘመናዊ ሰራዊት እንዲገነባ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርስቲ አስተማማኝ የሰላምና የልህቀት ተቋምነቱን በተግባር የሚያረጋግጡ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ለጎረቤት አገራት ተማሪዎች የትምህርት ዕድል በመስጠትም መልካም የዲፕሎማሲ ሥራን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 

ዩኒቨርስቲው አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን የጥናት ምርመር ሥራዎችን በማከናወን ውጤት ተኮር ሥራዎችን በማስመዝገብ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አኳያ፤ በግዳጅ ምክንያት ሕይወታቸውን ላጡ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ልጆች የትምህርት ዕድል እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል። 

በምርቃት መርኃ ግብሩ ላይ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች ሽልማት ተበርክቷል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በ2025 ከአፍሪካ አምስት ምርጥ የመከላከያ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የመሆን ራዕይ ሰንቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም