በድሬዳዋ ሲካሄድ የቆየው የአገራዊ ምክክር አጀንዳ የማሰባሰብ ተግባር አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ በማስረከብ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ ሲካሄድ የቆየው የአገራዊ ምክክር አጀንዳ የማሰባሰብ ተግባር አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ በማስረከብ ተጠናቀቀ
ድሬዳዋ፤ ነሐሴ 11/2016 (ኢዜአ)፡-በድሬዳዋ ለስድስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአገራዊ ምክክር አጀንዳዎችን የማሰብሰብ ተግባር የተደራጁትን አጀንዳዎች ለኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማስረከብ ዛሬ ተጠናቀቀ።
በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች፣ የኃይማኖት አባቶች ፣ የሲቪል ማህበራት እና ሌሎች ባለድርሻዎች ላለፉት ስድስት ቀናት በነፃነት እና በእኩልነት ተመካክረው ለአገራዊው ምክክር ያደራጇቸውን አጀንዳዎች አጠናቀው ለኮሚሽኑ አስረክበዋል።
በርክክብ ስነስርዓቱ ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር እንደተናገሩት ፤ በአጀንዳ ማሰባሰብ የተሳተፉት ባለድርሻ አካላት አገርን ከገጠማት ስብራቶች እና ችግሮች አውጥታ ወደ ብሩህ ጎዳና እንድትጓዝ በነፃነት እና በእኩልነት ያደራጇቸው አጀንዳዎች ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።
አጀንዳዎቹ በአገር መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር ፤ በአገር ደረጃ የገጠሙ ችግሮች በምክክር መፍትሄ እንዲያገኙ የሚያግዙ እና ለቀጣይ አገራዊ ምክክር የሚቀርቡ መሆናቸውን ገልጸዋል ።
ተሳታፊዎቹ በአጀንዳ ማሰባሰቡ ሂደት በመደማመጥ እና በመነጋገር ላበረከቱት አስተዋጽኦ ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ምስጋና አቅርበዋል።
የኮሚሽኑ ስራ የተደላደለ እንዲሆን የድሬደዋ አስተዳደር ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ላበረከተው አስተዋጽኦ የላቀ ምስጋና እናቀርባለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በመመካከር ፣ በመደማመጥ ፣ በህብረት በመሆን በአገሪቱ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር፣ ዘላቂ አንድነት እና የፀና ሰላም እንዲሰፍን የማመቻቸቱ ተግባራት በተደላደለ ስኬት እየተጓዙ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
በድሬዳዋ አጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት ላይ በነቃ ትጋት ኃላፊነታቸውን የተወጡ ባለድርሻዎች የዚህ ታላቅ ታሪክ አካል መሆናቸውንም በአፅንኦት ገልጸዋል።
በአምስት ቡድን የተዋቀረው የድሬዳዋ አስተዳደር አጀንዳ ሰብሳቢዎች የተሰማሙበትን ሆነ በልዩነት ያስቀመጧቸውን አጀንዳዎች ለኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረክበዋል ።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ የካቢኔ አባላት እንዲሁም የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ተገኝወርቅ ጌቱ(ዶ/ር) ተገኝተዋል ።