ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና በ20 አትሌቶች ትወከላለች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በፔሩ ሊማ በሚካሄደው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና በስድስት የውድድር አይነቶች 20 አትሌቶችን እንደምታሳተፍ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ሻምፒዮናው ከነሐሴ 21 እስከ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ይከናወናል።

በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ አትሌቶች ዝግጅቱን እያደረገ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገልጿል።

አትሌቶቹ ዛሬ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ልምምዳቸውን ማከናወናቸውን አመልክቷል።

ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በ800፣1500፣ 3000 እና 5000 ሜትር በሁለቱም ጾታዎች እንዲሁም በ10000 ሜትር እርምጃ እና በ3000 ሜትር መሰናክል በሴቶች ብቻ ትወዳደራለች።

በውድድሩ ላይ 11 ሴቶች እና 9 ወንዶች በድምሩ 20 አትሌቶች ይሳተፋሉ።

በ20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ከ134 አገራት የተወጣጡ 1 ሺህ 720 አትሌቶች እንደሚሳተፉ የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያመለክታል።

በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመምና የሜዳ ተግባራትን ያካተተና እድሜቸው ከ20 ዓመት በታች የሆኑ አትሌቶች የሚሳተፉበት ውድድር ነው።

ውድድሩ ከእ.አ.አ. ከ1986 ጀምሮ የዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሚል ስያሜ ሲካሄድ ቆይቶ እ.አ.አ 2015 የስያሜ ለውጥ በማድረግ የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሚል እየተደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም