ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የንግድና የኢንቨስትመንት ከባቢዋን ምቹ ለማድረግ የምታከናውናቸው ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የንግድና የኢንቨስትመንት ከባቢዋን ምቹ ለማድረግ የምታከናውናቸው ሥራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን የተ.መ.ድ የንግድና ልማት ድርጅት ገለጸ። 

የድርጅቱ የአፍሪካ ቀጣናዊ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዲያን ሳይንዞጋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የንግድና የኢንቨስትመንት ከባቢዋን ምቹ ለማድረግ የምታከናውናቸው ሥራዎች የሚበረታቱ ናቸው። 

ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ኃብትና የሰው ኃይል ተጠቅማ ዜጎቿን ከድኅነት ከምታወጣባቸው መንገዶች አንዱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሆኑንም ገልጸው ኢትዮጵያም በዚህ ዘርፍ  የምታከናውነው ሥራ የሚደነቅ ነው ብለዋል። 

ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ጨምሮ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የምታከናውናቸው የፖሊሲ ማሻሻያዎች የአገሪቱን አጠቃላይ የኢንቨስትመንትና የንግድ ሥራ ውጤታማ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲም በተለይም ከዚህ ቀደም በዘርፉ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት የተሻለ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንደሚያደርጋት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። 

አገሪቱ በፈጣን የለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗም በርካታ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ  ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።  

አገሪቷ በተለይም  የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ በተለያዩ ዘርፎች እያደረገቻቸው ያሉ ማሻሻያዎች  የመንግሥትን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ መሆኑንም አስረድተዋል።

የተ.መ.ድ የንግድና ልማት ድርጅት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግና ኢኮኖሚውን ለመደገፍ የተለያዩ የቴክኖክና ፋይናንስ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም