ቀጥታ፡

በዲላ ከተማ የኮሪደር ልማት የሚከናወንበትን የአስፓልት መንገድ ግራና ቀኝ ነጻ የማድረግ ሥራ እየተፋጠነ ነው

ዲላ፤ ነሐሴ 11/2016(ኢዜአ)፦ በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ የኮሪደር ልማት የሚከናወንበትን የአስፓልት መንገድ ግራና ቀኝ ነጻ የማድረግ ሥራ እየተፋጠነ መሆኑን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ዳንኤል ሽፈራው ለኢዜአ እንደገለጹት የዲላን ከተማን ደረጃ ለማሻሻል ህብረተሰቡን በማሳተፍ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው።

ልማቱ በተለይ ከተማዋን ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ ያረጁ አካባቢዎችን መልሶ የማልማትና በዋና ዋና መንገዶች የእግረኛ መንገድ ግንባታን ማካተቱን አመልክተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ከፈታ እና ደረጃ የማሻሻል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ነው የጠቀሱት።

በአሁኑ ወቅትም በከተማው ከሚችሌ ጀግኖች አደባባይ እስከ ጪጩና ሆስፒታል ማዞሪያ ድረስ የኮሪደር ልማት ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።

በዚህም ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ ዋና ዋና የአስፓልት መንገድ ግራና ቀኝ ነጻ የማድረግ ሥራ እየተፋጠነ መሆኑን ነው ከንቲባው አቶ ዳንኤል የተናገሩት።

እንደእሳቸው ገለጻ፣ የኮሪደር ልማቱ የእግረኛ እና የሳይክል መንገድ፣ የአረንጓዴ ልማት እንዲሁም የማረፊያ ስፍራዎችን የሚያካትት ነው።

ለኮሪደር ልማቱ ይዞታን ነጻ የማድረግ ሥራው በህብረተሰቡ ተሳትፎ ጭምር እየተከወነ መሆኑን አቶ ዳንኤል ገልጸው፣ ልማቱ የከተማዋን ፕላን ለማስጠበቅ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የከተማዋን ተወዳዳሪነትና ተመራጭነት ያሳድጋል ያሉት ከንቲባው፣ የትራንስፖርት ፍሰቱን በማሳለጥ ነዋሪውን በተሻለ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

ከተማዋን ለማሳደግ በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ነዋሪው እያደረገ ያለውን ተሳትፎ እንዲያጠናክርም ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል።

በከተማው ለሚከናወነው የኮሪደር ልማት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከ14 ኪሎ ሜትር በላይ ይዞታን ነጻ ለማድረግ መቻሉን የገለጹት ደግሞ የዲላ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ምንተስኖት ከበደ ናቸው።

የተቀሩ አካባቢዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ነጻ በማድረግ በቀጣይ ሦስት ወር ጊዜ ውስጥ የኮሪደር ልማቱን እውን ለማድረግ በርብርብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕላን ለከተሞች እድገት መሰረት መሆኑ ያነሱት ሥራ አስኪያጁ፣ ህብረተሰቡ ይህንን በመገንዘብ አስፈላጊውን ትብብር እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ለልማቱ ይዞታቸው ነጻ ያደረጉ የከተማው ነዋሪዎች በበኩላቸው አስተዳደሩ የተጀመረውን የኮሪደር ልማት በተያዘለት ጊዜ እውን እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ከነዚህ ነዋሪዎቹ መካከል በከተማው በሆቴል አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩት አቶ እዩኤል ሽፈራው  የኮሪደር ልማቱ ለከተማው ዕድገት ወሳኝ መሆኑን በመረዳታቸው ይዞታቸውን በፍጥነት ነጻ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በተለይ የከተሞች እድገት ለሆቴል አገልግሎት ዘርፍ የተለያየ ጠቀሜታ ስላለው ለልማቱ አውን መሆን ድጋፋቸውን አጠናክርው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።


 

የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በከተማው በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ደስተኛና ተባባሪ መሆናቸውን ያነሱት ደግሞ ሌላኛው የከተማው ነዋሪ መቶ አለቃ ሲሳይ ዳሪሎ ናቸው።

በከተማ አስተዳደሩ ጥያቄ መሰረት ከ3 ሜትር በላይ ይዞታቸውን ነጻ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም