የታክስ ሥወራን ጨምሮ ከልዩ ልዩ ወንጀሎች ጋር ተያይዞ ከ5 ሺህ በላይ መዝገቦች ለዐቃቤ ሕግ ተላልፈዋል - ኢዜአ አማርኛ
የታክስ ሥወራን ጨምሮ ከልዩ ልዩ ወንጀሎች ጋር ተያይዞ ከ5 ሺህ በላይ መዝገቦች ለዐቃቤ ሕግ ተላልፈዋል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2016(ኢዜአ)፦በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት በታክስ ሥወራ፣ በግብር ማጭበርበር፣ ያለደረሰኝ ግብይት በመፈጸምና ሐሰተኛ ማስረጃ ከመጠቀም ጋር ተያይዞ ከ5 ሺህ በላይ መዝገቦች ለዐቃቤ ሕግ መተላለፋቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገለጸ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራልና የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ዘላለም መንግሥቴ፤ በታክስ ሥወራ፣ ግብር ማጭበርበር፣ ያለደረሰኝ ግብይትና ሐሰተኛ ማስረጃ ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
አገርና ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ወንጀሎችን በመመርመር ተገቢው የሕግ እርምጃ እንዲወሰድ የማድረግ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአብነትም በአፍሪካ ኅብረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ከፍተኛ መጠን ያለው አሜሪካን ዶላር ለማውጣት የነበረውን ሙከራ በማክሸፍ የምርመራ ሂደቱን በማጠናቀቅ ተጠርጣሪዎች ማረሚያ ቤት ወርደው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ መሆኑን አንስተዋል።
በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጸሙ አሻጥሮችን በመቆጣጠር ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው ለአብነትም ከ25 ቢሊየን ብር በላይ በመንግሥትና በሕዝብ ኃብት ላይ ጉዳት ያደረሱ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራቸው እየተጣራ መሆኑን ገልጸዋል።
በድምሩም ከ5 ሺህ በላይ መዝገቦች ምርመራቸው ተጠናቆ ለዐቃቤ ሕግ መተላለፋቸውን ነው ያስረዱት።
በአገር ኢኮኖሚ ላይ አሻጥር ለመፈጸም ሁኔታውን እየቀያየረ የሚገኘውን የወንጀል ተግባር ለመቆጣጠር ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በመተባበር በዕውቀትና ቴክኖሎጂ የተመሰረተ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
መንግሥት በተለያየ ሁኔታ የተወጠረ የሚመስላቸው አካላት ትክክለኛ የሚመስል ሐሰተኛ ማስረጃን በማዘጋጀት በኮንቲነር ጭምር ምርትን ወደ አገር ቤት ለማስገባት የሞከሩ አካላት መኖራቸውን ገልጸዋል።
በሌለ የንግድ ድርጅት ሐሰተኛ መታወቂያና የንግድ ሥርዓት መስፈርቶችን በመጠቀም በአገር ኢኮኖሚ አሻጥረኞች ላይ በፎረንሲክ ምርመራ በማጣራት ወንጀሉን የመከላከል ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል።
ሕዝብና መንግሥት የሰጣቸውን አደራ ወደጎን በመተው በሌብነት ተግባር በተሰማሩ የመንግሥትና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችም ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርቡ የተቋማት ኦዲት ሪፖርት ጉድለቶችን መነሻ በማድረግ የሕዝብና መንግሥት ኃብትን ላልተገባ ዓላማ ባዋሉ የሥራ ኃላፊዎችንም ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
እየተገነባ ያለው የፌደራል ፖሊስ የዓለም አቀፍ የፎረንሲክ ምርመራ ማዕከል ሲጠናቀቅ የሕግ-የበላይነትን በማስከበር የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ የሚያስችል ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ማዕከሉም ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ አገራት ጭምር በዘርፉ የልህቀት ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል ታስቦ በዘመናዊ መንገድ እየተገነባ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስን በዕውቀትና ቴክኖሎጂ የሚመራ አስተማማኝ ተቋም በማድረግ ወንጀልን የመከላከል፣ ሰላምና ደኅንነትን በማስጠበቅ ፍትሕ የማረጋገጥ ኃላፊነቱን በብቃት ለመወጣት ተከታታይ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።