ቀጥታ፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህጋዊ የንግድ ስርዓትን በማጠናከር የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ቡታጅራ፤  ነሐሴ 11 /2016 (ኢዜአ)፡- .በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህጋዊ የንግድ ስርዓትን በማጠናከር የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት  የሚያጎብቱ ተግባራት  እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው ገለጹ።

የቢሮው የ2016 በጀት ዓመት ስራ አፈጻጸም ግምገማና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የሚመክር መድረክ  ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በተገኙበት  በቡታጅራ  ከተማ  እየተካሄደ ነው።


 

በመድረኩ ላይ  የቢሮው ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው እንዳሉት፤በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት  በክልሉ ህጋዊ የንግድ ስርዓትን በማጠናከር ዜጎች በተረጋጋ ግብይት ተዋናይ እንዲሆኑ የተደረገው ጥረት ውጤታማ ነው።

ወደ ህጋዊ መስመር ያልገቡ  ነጋዴዎችን ስርዓት የማስያዝና  ህገወጥ ንግድን መቆጣጠር እንዲሁም ገበያን ማረጋጋት የሚያስችሉ ጠንካራ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በ2016 የበጀት ዓመት ከ42 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ወደ ህጋዊ የንግድ ስርዓት እንዲገቡ መደረጉንም ጠቅሰዋል።

ህገ ወጥነትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት  56 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይትና ከ134 ሺህ ኩንታል በላይ የምግብ እህል በህገ ወጥ መንገድ ተሸሽጎ መቆጣጠር መቻሉንም  ጠቁመዋል።

በተቋቋመው ግብረ ኃይል አማካኝነት በቁጥጥር ስር የዋለው ምርትም  ለማህበረሰቡ ማቅረብ መቻሉን አስረድተዋል።

እንዲሁም ገበያን ለማረጋጋት  104 የቅዳሜና እሁድ  ገበያዎችን ማቋቋም ስለመቻሉና በዚህም ሸማቹ በቀጥታ ምርት እንዲያገኝ መደረጉንም አመልክተዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ የምርት መሸጫ ያልተገባ  ዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 700 የሚጠጉ የንግድ ተቋማት  የተለያዩ ህጋዊ እርምጃዎች እንደተወሰደባቸውም አቶ ዳንኤል ተናግረዋል።

ቢሮው በህገ ወጥ መንገድ ምርቶችን የሚያከማቹና ዋጋ በሚጨምሩ አካላት ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥርና እርምጃ ያጠናክራል ብለዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ እንዳሻው ጣሰው በተገኙበት እየተካሄደ በሚገኘው መድረክ በዘርፉ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አካላት እወቅናና ሽልማት እንደሚሰጥም ተገልጿል።

በመድረኩ ላይ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ስርሞሎ፣ የክልሉ  ዋና የመንግሥት ተጠሪ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር)ን ጨምሮ  ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም