የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ዛሬ መካሄድ ይጀምራል።
በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ ከዘጠኝ አገራት የተወጣጡ ዘጠኝ ክለቦች ይሳተፋሉ።
ኢትዮጵያን በሴካፋ ዞን ወክሎ በማጣሪያ ውድድሩ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በምድብ 1 ከኬንያው ኬንያ ፖሊስ ቡሌትስ፣ ከሩዋንዳው ራዮን ስፖርትስ፣ ከደቡብ ሱዳኑ ዬ ጆይንት ስታርስና ከዛንዚባሩ ዋሪየር ኩዊንስ ጋር ተደልድሏል።
የታንዛኒያው ሲምባ ኩዊንስ፣ የብሩንዲው ፒቪፒ ቡዬንዚ፣ የዩጋንዳው ካዌምፔ ሙስሊምና የጅቡቲው ፋድ በምድብ 2 የተደለደሉ ክለቦች ናቸው።
ውድድሩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሩዋንዳው ራዮንስ ስፖርት ከቀኑ 9 ሰዓት በአዲስ አበባ በቂላ ስታዲየም በሚያደርገው ይጀመራል።
መርሐ ግብሩ ነገም ቀጥሎ ሲውል በምድብ 1 ኬንያ ፖሊስ ቡሌትስ ከደቡብ ሱዳኑ ዬ ጆይንት ስታርስ ጋር ከቀኑ 9 ሰዓት በአበበ በቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የሴካፋ ዞን ማጣሪያ እስከ ነሐሴ 26 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በማጣሪያ ውድድሩ የሚሳተፈው የዘንድሮው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ነው።
ክለቡ ከዚህ ቀደም ባደረጋቸው ሶስት ተሳትፎዎች በሁለቱ ፍጻሜ ደርሶ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። ባስመዘገባቸው ውጤቶች ለካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ማለፍ አልቻለም።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድሩን ካሸነፈ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ የሚሳተፍ ይሆናል።