የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት የቅፅበታዊ አደጋ ስጋት ምላሽ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ አስቀመጠ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት የቅፅበታዊ አደጋ ስጋት ምላሽ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ አስቀመጠ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የቅፅበታዊ አደጋ ስጋት ምላሽ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ አስቀመጠ።
ምክር ቤቱ በድሬዳዋ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የክረምቱ ዝናብ ከባድ መሆኑን ተከትሎ በደረሱ ቅፅበታዊ የናዳና ጎርፍ አደጋዎች እንዲሁም የሰብዓዊ ድጋፍ ምላሽ ላይ ተወያይቷል።
የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፥ በክረምቱ ከባድ ዝናብ በተከሰቱ ቅፅበታዊ አደጋዎች የበርካታ ዜጎቻችንን ህይወት አጥተናል ብለዋል።
አደጋው ከዚህ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ የተደረገው ርብርብ መልካም ቢሆንም፥ አደጋ አይቀሬ በመሆኑ ይህንን መቋቋም የሚያስችል ስርዓት መገንባት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የአደጋ ስጋት አመራር መንግሥታዊ መዋቅሮችን መተፈተሽና ለአደጋዎች በቂ ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም እንዲኖራቸው ማድረግ ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል።
ምክር ቤቱ በቀጣይ በትኩረት የሚሠራባቸውን አቅጣጫዎች ያስቀመጡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ቅፅበታዊ አደጋዎች አሁንም ሊከሰቱ እንደሚችሉ የትንበያ መረጃዎች ስለሚያሳዩ አደጋን የመከላከል ተከታታይ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
ለዚህም ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ያሉ ዜጎችን የማስገንዘብና እንደአስፈላጊነቱም ከስፍራው የማንሳት ሥራ ያስፈልጋል ብለዋል።
በአደጋዎቹ ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚደረገው ድጋፍና እርዳታ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግም የቀጣይ ትኩረታችን ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በነበሩ ግጭቶች በየአካባቢው ተፈናቅለው የሚገኙ ዜጎችን የመመለስና በዘላቂነት የማቋቋም ሥራ ከክልሎች ጋር በመቀናጀት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የተረጂዎችንና ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን ትክክለኛ መረጃ ማጥራትና ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ለአደጋ ጊዜ ምላሽ የሚሆን የሀብት ማሰባሰብ ጅምሮችን አጠናክሮ ማስቀጠል የሁሉም ትኩረት መሆን እንዳለበትም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ፥ የክረምቱ ዝናብ በላሊና ምክንያት ከባድ እንደሚሆን ከግንቦት ጀምሮ መተንበዩን አውስተዋል።
እስከ መስከረም ድረስ ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰው፥ በዓባይ፣ አዋሽ፣ ባሮ አኮቦና ሌሎች ተፋሰሶች ያሉ ዜጎች ለጎርፍ መጥለቅለቅ ስጋት አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር)፥ በዘንድሮው ክረምት ከወትሮው የተለዩ ከባድ ቅጽበታዊ አደጋዎች መፈጠራቸውን ገልጸዋል።
ለጎርፍና ለመሬት ናዳ ተጋላጭ በሆኑ የወንዝ ተፋሰስና ተዳፋት ቦታዎች ያሉ ዜጎችን ከቀያቸው ማንሳት መጀመሩን ገልጸው፥ አሁንም አመራሩ ይህንን ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ተናግረዋል።
ህብረተሰቡም ቅድመ ማስጠንቀቂያዎችን ተግባራዊ እንዲያደርግና ራሱን ከአደጋ ሊጠብቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ምክር ቤቱ በራስ አቅም ሰብዓዊ ድጋፍን የመሸፈን ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አቅጣጫ አስቀምጧል።