የኮደሮች ሥልጠና ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በቴክኖሎጂ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ገበያ ያላቸውን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኮደሮች ሥልጠና ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በቴክኖሎጂ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ገበያ ያላቸውን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 11/2016(ኢዜአ)፦ የኮደሮች ሥልጠና ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በቴክኖሎጂ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ገበያ ያላቸውን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ መሆኑ ተገለጸ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ይፋ የተደረገው የ''አምስት ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ’’ በኢትዮጵያና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግሥታት የተጀመረ የዲጂታል ሥራ ክህሎትን የማሳደጊያ የትብብር ፕሮጀክት ነው።
ወጣቱ የቴክኖሎጂ እውቀቱን በማዳበር በተለያዩ ዓለማት ተንቀሳቅሶ የመሥራት አቅምን የሚሰጠው ይኸው ፕሮጀክት "ትውልድ ይማር፣ ትውልድ ይሰልጥን፣ ከዓለም ጋር ይፎካከር" በሚል እሳቤ በመተግበር ላይ ይገኛል።
ፕሮጀክቱ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት የሚተገበር ሲሆን 5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታ ሳይንስና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት እንዲጨብጡ ያስችላል ተብሏል።
ፕሮጀክቱ ወጣቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው የሙያ ሰርቲፊኬት ለማግኘት እንደሚያስችላቸውም ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የኤሌክትሪካልና ኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ ምሁርና የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ከማል ኢብራሂም (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኮዲንግ የተለያዩ መተግበሪያዎች በሚሰጣቸው ትዕዛዝ መሠረት ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ ማድረጊያ ዘዴ ነው።
በዚህ ዲጂታል ዘመን ጥቅም ላይ የሚውሉ መተግበሪያዎች እንደ ከዚህ ቀደም በመገጣጠም ሳይሆን በሚሰጣቸው ትዕዛዝ ወይንም ኮዲንግ አማካኝነት ተግባራቸውን እንዲፈጽሙ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በዚህም ኮዲንግ የዘመኑ የሁሉ ነገሮች ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን ያነሱት ምሁሩ፤ የዚህ ክህሎት ባለሙያ መሆን ተወዳዳሪነትን የሚጨምርና ተፈላጊነትን የሚያሳድግ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኮዲንግን መጠቀም በርካታ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ ጠቁመው፤ በኮዲንግ የሚሰሩ ሥራዎች ትክክልና ወጪ ቆጣቢ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በኮዲንግ የሚከናወኑ ሥራዎች በተደጋጋሚ ሙከራ ተፈትሸው የሚወጡ በመሆናቸውም ያላቸው ተቀባይነት ከፍ ያለ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኮዲንግ ሥልጠናን መከታተል ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታን ያስገኛል የሚሉት ምሁሩ ተወዳዳሪነትን በመጨመር የሥራ ዕድልን የሚያሰፋ መሆኑንም ተናግረዋል።
የወጣቶችን እውቀት ከፍ በማድረግም በዲጂታል ዘርፍ ችግር ፈቺ ሥራዎችን እንዲሰሩ የሚያስችል ታላቅ ዕድል መሆኑንም ገልፀዋል።
በኮዲንግ ሥልጠና መሳተፍ ራስን ከመቀየር ባሻገር አገርን ለመጥቀም ትልቅ ዕድል መሆኑንም ጠቁመው፤ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በሥልጠናው መሳተፍ እንዳለባቸው መክረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ ሰለሞን አማረ፤ በሦስት ዓመት ሥልጠናው በከተማ አስተዳደሩ 300 ሺህ ወጣቶች ተሳታፊ ይሆናሉ ብለዋል።
በዚህም በ2017 በጀት ዓመት 75 ሺህ ወጣቶች ሥልጠናውን እንዲከታተሉ ዕቅድ መያዙን ጠቁመው፤ በሐምሌና ነሐሴ ብቻ 60 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች ሥልጠናውን በመከታተል ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከዚህም ውስጥ 28 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች አንድና ሁለት የሥልጠና መርኃ-ግብሩን አጠናቀው ሰርቲፊኬት መውሰዳቸውን ጠቁመዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሹሩን አለማየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኮዲንግ ሥልጠናው በበይነ-መረብ "ዩዳሲቲ" በተሰኘ ተቋም እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ሥልጠናው ዲጂታል ኢኮኖሚን መገንባት የሚያስችልና ክህሎት ያለውን ማኅበረሰብ መፍጠር ዓላማ ያነገበ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአገር አቀፍ ደረጃ እስካሁን ከ95 ሺህ በላይ ወጣቶች ሥልጠና በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
በሦስት ዓመት ሥልጠናው እያንዳንዱ ክልልና የከተማ አስተዳደር ማሰልጠን ያለባቸውን የሰው ኃይል መመደቡን ጠቁመው፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችም የእረፍት ጊዜያቸውን አጠናቀው ሲመለሱ የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
ለሥልጠናው መሳካትም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የ''አምስት ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ’’ ሥልጠና በኢትዮጵያና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግሥታት የተጀመረ ሲሆን፤ ለስድስት ሳምንታት በሚሰጥ ሥልጠና ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ሰርቲፊኬት የሚገኝበት ነው።