የክልሉ የጸጥታ ኃይል ከፌዴራል የጸጥታ ኃይል ጋር በመሆን አካባቢውን ለመጠበቅና እርምጃ ለመውሰድ በቂ ዝግጅት አለው- የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉ የጸጥታ ኃይል ከፌዴራል የጸጥታ ኃይል ጋር በመሆን አካባቢውን ለመጠበቅና እርምጃ ለመውሰድ በቂ ዝግጅት አለው- የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10/2016(ኢዜአ)፦የክልሉ የጸጥታ ኃይል ከፌዴራል የጸጥታ ኃይል ጋር በመሆን አካባቢውን ለመጠበቅና እርምጃ ለመውሰድ በቂ ዝግጅት አለው ሲል የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም ክልሉ አንድ ዓመት በሞላው የሰላም እጦት ውስጥ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
ከሐምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ክልሉ እስከ አሁን ድረስ የሰላም መደፍረስ ችግር አጋጥሞት መቆየቱን ነው የተናገሩት፡፡
የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ ለመቀየር መንግሥት በርካታ የሰላም አማራጮችን ማቅረቡን የተናገሩት ምክትል ሃላፊው ሰላማዊ ውይይቶች ሲተገብሩ መቆየታቸውን ነው የተናገሩት፡፡
ጥያቄ እና ሃሳብ አለኝ የሚል እንዲቀርብ እና ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ጥረት መደረጉንም አስታውሰዋል፡፡
የሰላም ጥረቱን ወደ ጎን የገፉ የታጠቁ ኃይሎች በክልሉ ቀውስ መፍጠራቸውንም ተናግረዋል፡፡
በፈጠሩት ቀውስ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ ሃብት እና ንብረት ወድሟል፣ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ተመሰቃቅለዋል፣ ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ተወዳዳሪ እንዳንኾን አድርጓል፣ ለክልሉ የማይመጥን ሁኔታዎችን ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡
የክልሉን የጸጥታ ኃይል መልሶ በማደራጀት እና በማሠልጠን የጸጥታ ችግር የነበረባቸውን አካባቢዎች ወደ ሰላም ለመመለስ ሥራ መሠራቱንም አንስተዋል፡፡
አካባቢዎችን ከታጠቁ ኃይሎች ነጻ ከማድረግ ጎን ለጎን የሕዝብን የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን የመፍታት ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል፡፡
ከሰሞኑ የታጠቁ ኃይሎች ከተሞችን ያነጣጠረ ጥቃት ለመፈጸም ሙከራ እያደረጉ መሆናቸውን የተናገሩት ምክትል ሃላፊው ከተሞች ላይ በማፈንዳት፣ ንጹሕንን በመግደል፣ በማገት ኅብረተሰቡ ከገባበት ቀውስ እንዳይወጣ ተዳጋጋሚ ችግሮችን እየፈጠሩ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
ለሃይማኖት አባቶች፣ ለሀገር ሽማግሌዎች ክብር እንደማይሰጡም ገልጸዋል፡፡
ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም ከእኩለ ቀን በኋላ በተነዛው ሃሰተኛ መረጃ በባሕር ዳር ከተማ ሱቆች እንዲዘጉ፣ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት አገልግሎት እንዳይሰጡ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡
ማኀበረሰቡ በሃሰተኛ መረጃዎች መሸበር እና ሥራውን ማቆም እንደሌለበትም አሳስበዋል፡፡
የክልሉ እና የፌዴራል የጸጥታ ኃይል በቂ ዝግጅት ማድረጉን የተናገሩት ምክትል ሃላፊው ከተማ ዝም ተብሎ የሚገባበት አይደለም ብለዋል፡፡
በከተማዋ ውስጥ ፍንዳታ የፈጸሙ አካላት የተወሰኑት በቁጥጥር ሥር ውለዋል፤ ሌሎችንም ለመያዝ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ኅብረተሰቡ በሃሰተኛ መረጃዎች ሱቆችን መዝጋት፣ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዳይኖር ማድረግ ማቆም እንደሚገባውም አስገንዝበዋል፡፡
አካባቢው እንዲተራመስ የሚነዛውን ሃሰተኛ ወሬ ወደ ጎን በመተው ከመንግሥት ጋር በመቆም ሰላሙን ለማረጋገጥ ይገባዋል ብለዋል፡፡
የሚዘርፍ፣ ምጣኔ ሃብትን የሚያደቅ፣ የሕክምና እና የትምህርት አገልግሎት እንዳይሰጥ የሚያደርግ፣ ሕይወትን የሚያወሳስብ ቡድን ለሕዝብ ጠላት እንጂ ወዳጅ አይደለም ነው ያሉት፡፡
ማኀበረሰቡ ተው በማለት መገሰጽ እና ሰላሙን ማስጠበቅ ይገባዋል ብለዋል፡፡
የክልሉ የጸጥታ ኃይል ከፌዴራል የጸጥታ ኃይል ጋር በመሆን አካባቢውን ለመጠበቅ እና ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ በቂ ዝግጅት አለው ነው ያሉት፡፡
ወደ ሰላም አማራጭ የሚመጣ ካለ መምጣት ይችላል፤ ከዚህ ውጭ የሆነ አካሄድ ካለ ግን እርምጃ ለመውሰድ እና ለማስተካከል የሚያስችል በቂ ዝግጅት አድርገናል ነው ያሉት፡፡
ማኀበረሰቡ ወደ ኋላ የሚመልስ፣ አውዳሚ አስተሳሰብ መቃወም እንደሚጠበቅበትም ተናግረዋል፡፡
የታጠቁ ኃይሎች ለሃሰተኛ መረጃ ማሰራጫነት የሚገለገሉባቸው ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ የተዘረጉ ሃሰተኛ ሚዲያዎች መኖራቸውን የተናገሩት ሃላፊው በሃሰተኛ ማሠራጫዎቹ አማካኝነት ባሕር ዳርን ተቆጣጠርን እያለ እያስወራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተደጋጋሚ ስለ ባሕር ዳር ሃሰተኛ መረጃዎች ተሰራጭተዋል፣ ባሕርዳር ላይ የተፈጠረ ምንም ነገር የለም፣ ኅብረሰተቡ በሃሰተኛ መረጃ ተደናግሮ ሱቅ መዝጋት፣ ሥራውን ማቆም አይገባው ነው ያሉት፡፡
ከተማ ዘው ብሎ መቆጣጠር የሚያስችል አቅምም ብቃትም የለውም፣ የጸጥታ ኃይሉ በቂ ዝግጅት አድርጓል፣ ይሄን ማረጋገጥ አፈልጋለሁ ነው ያሉት፡፡
የታጠቁ ኃይሎች አካሄድ ለሀገር የማይጠቅም፣ ሀገርን ወደ ኋላ የሚመልስ ነው ብለዋል፡፡ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ከዚህ በኋላ በቃን ልጆቻችን ልታስጨርሱ ነው፣ ግጭቱ ተገቢ አይደለም፣ ሕይወታችንን እያወሳሰበ ነው በማለት እየተቃወመ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ሰላም ወዳድ ነው፣ ለሰላሙ መከበር ከመንግሥት ጋር የሚሠራውን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡ በሃሰተኛ መረጃ መረበሽ እና ሥራን ማቆም፣ ፈጽሞ ሊኾን አይገባም፣ መስተካከል አለበት ነው ያሉት፡፡
መንግሥት ለሰላም ያለውን ዝግጁነት እና ቁርጠኝት በተደጋጋሚ አሳይቷል፤ የታጠቀው ኃይል ራሱን ለውይይት አዘጋጅቶ እስከ መጣ ድረስ በራችን ክፍት ነው፣ በኃይል ለመጣ ግን እርምጃ ለመውሰድ ብቁ ዝግጅትም፣ ብቃቱም አለን ማለታቸውን የአሚኮ ዘገባ ያሳያል።