ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የቦክስ ውድድር የአገሪቱን የቦክስ ስፖርት ለማነቃቃት ይረዳል 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10/2016(ኢዜአ)፦  በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የቦክስ ውድድር የአገሪቱን የቦክስ ስፖርት ለማነቃቃት እንደሚረዳ ተወዳዳሪዎች ገለፁ።

የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ምርጫ ኅዳር 8 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ መከናወኑ ይታወሳል።

በዚህም ምርጫ ኢትዮጵያዊው አቶ ኢያሱ ወሰን አሸንፈው የአፍሪካን የቦክስ ስፖርት እየመሩ መሆናቸው የሚታወስ ነው።

በአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ዋና ጽሕፈት ቤት መቀመጫ፤ ምርጫውን ባሸነፈው ግለሰብ አገር በመሆኑ ወደ ኢትዮጵያ መጥቷል።

የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ዋና ጽሕፈት ቤት በአዲስ አበባ ይፋ የሚደረግበትን ቀን ምክንያት በማድረግ፤ ዓለም አቀፍ የቦክስ ሻምፒዮና በነገው ዕለት በአዲስ አበባ በአድዋ ሙዚየም ይከናወናል።

በዚህ ውድድር ኢትዮጵያ በ60 ኪሎ ግራም በአቡበከር ሰፋን እና በ75 ኪሎ ግራም ደግሞ በተመስገን ምትኩ አማካኝነት የምትወዳደር ሲሆን፤ በዛሬው ዕለትም በአዲስ አበባ በአድዋ ሙዚየም የተወዳዳሪዎች ኪሎ የመለካትና የእርስ በርስ የትውውቅ መድረክ ተከናውኗል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የቦክስ ውድድር የአገሪቱን የቦክስ ስፖርት ለማሳደግ ፋይዳው የጎላ ነው።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ክለብና የኢትዮጵያ የቦክስ ብሔራዊ ቡድን ተወዳዳሪ የሆነው ተመስገን ምትኩ፤ ውድድሩ በኢትዮጵያ መዘጋጀቱ ለተወዳዳሪዎች የውድድር አማራጭ እንደሚፈጥር ገልጿል።

ኢትዮጵያውያን የቦክስ ተወዳዳሪዎች በአገር ውስጥ ብቻ ሳይወሰኑ፤ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረክ እንዲያገኙ ያደርጋል ሲል ተናግሯል። 

ውድድሩ በአድዋ ሙዚየም መደረጉ ለአገሪቱ ገፅታ ግንባታ የራሱ አስተዋፅዖ እንዳለው ነው የገለጸው።

የፌደራል ማረሚያ ቤቶችና የኢትዮጵያ የቦክስ ብሔራዊ ቡድን ተወዳዳሪ የሆነው አቡበከር ሰፋን በበኩሉ፤ ውድድሩን ኢትዮጵያ ማዘጋጀቷ የአገሪቱን ቦክስ በበጎ ጎኑ ያነቃቃዋል ብሏል።

በውድድሩም ላይ የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች ከተለያዩ አገራት የሚመጡ በመሆናቸው ልምድ እንደሚያገኙበትም ገልጿል።

በአጠቃላይ ውድድሩ የተቀዛቀዘውን የቦክስ ስፖርት የሚያነቃቃ ስለሆነ፤ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው ቦክሰኞቹ የተናገሩት። 

ዓለም አቀፍ የቦክስ ውድድሩ በስድስት ምድቦች ተከፍሎ የሚከናወን ይሆናል።

በውድድሩም የተፋላሚ አገራት ምድብ የተለየ ሲሆን፤ በ73 ኪሎ ግራም ሞዛምቢክ ከናይጄሪያ፣ በ60 ኪሎ ግራም ጋና ከኢትዮጵያ፣ በ75 ኪሎ ግራም ኢትዮጵያ ከሞሮኮ ውድድራቸውን ያደርጋሉ።

በ48 ኪሎ ግራም ደግሞ ካዛኪስታን ከኡዝቤክስታን፣ በ79 ኪሎ ግራም ታንዛኒያ ከዴሞክራቲክ ኮንጎ እንዲሁም በ51 ኪሎ ግራም ጋና ከዛምቢያ ይፋለማሉ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም