ቀጥታ፡

በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የሚከናወኑ ተግባራት ለቀጣይ ትውልድ የሚተርፉ ናቸው 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10/2016(ኢዜአ)፦ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የሚከናወኑ ተግባራት ለቀጣይ ትውልድ የሚተርፉ ሥራዎች መሆናቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽኅፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ። 

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ ተከትሎ በፓሪስ ኦሎምፒክ የድል ባለቤት የሆኑ አትሌቶችን ጨምሮ አርቲስቶች፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል ዛሬ ችግኝ ተክለዋል።  

በመርኃ ግብሩ ተሳታፊዎች መካከል ችግኝ በፍጥነት የመትከል ውድድሮችና ሌሎችም ሁነቶች ተከናውነዋል።  

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽኅፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም እንደገለፁት፤ አረንጓዴ አሻራ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ ሥጋትን ከመከላከል አንጻር የማይተካ ሚና ይጫወታል። 


 

የአረንጓዴ አሻራ ተግባራት የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባሻገርም ጽዱ፣ ውብና ጤናማ አካባቢን ለትውልድ ለማስተላለፍ መሰረት መሆኑን ተናግረዋል። 

ባለፉት ዓመታት የአገሪቱን የደን ሽፋን ለመጨመር ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ የተሳተፉ ዜጎች የትልቅ ታሪክ አካል ናቸው ሲሉም ጠቁመዋል። 

በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ የሚከናወኑ ተግባራት ለትውልድ መሥራት መሆኑንም ነው ያስረዱት።  

ሁሉም ኅብረተሰብ የአረንጓዴ አሻራውን በማሳረፍ የዜግነት ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።

በችግኝ ተከላ መርኃ ግብሩ የተሳተፈው አትሌት ታምራት ቶላ በድሉ ማግስት የአረንጓዴ አሻራውን በማሳረፉ መደሰቱን ተናግሯል። 


 

ችግኞችን መትከል አትሌቶች የልምምድ መርኃ ግብራቸውን አረንጓዴ የተላበሰ ሥፍራ ላይ ለማከናወንም ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው ጠቁሞ ንጹህ አየር ለማግኘት እንደሚረዳ ገልጿል። 

አትሌት ለሜቻ ግርማ በበኩሉ ችግኝ ለሰው ልጅ ሕይወት በመሆኑ ሁሉም ዜጋ መትከል እንዳለበት ተናግሯል።  

የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር እውን የሚሆነው በሁሉም ተሳትፎ ነው ብሏል።  

አርቲስት ጥላሁን ጉግሳ በበኩሉ በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብሮች ለአየር ንብረት ለውጥ በጎ ሚና ማሳየታቸውን ገልጿል። 

ችግኞችን ከመትክል ባለፈ መንከባከብ እንደሚገባም ነው መልዕክቱን ያስተላለፈው።  

ጋዜጠኛ ስሜነህ ባይፈርስ፤ የአረንጓዴ አሻራ ለሰው ልጅ እስትንፋስ መሆኑን ገልጾ ያለ አረንጓዴ ልማት ሌሎች ልማቶችን ማከናወን አይቻልም ብሏል።

በየዓመቱ የሚከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብሮች ቀጣይነት ኖሯቸው ለትውልድ መተላለፍ እንዳለባቸውም ነው የገለጸው።   

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ነሐሴ 17፣ 2016 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ዓሻራችንን እናኑር ብለዋል።  

በአንድ መንፈስ በመላው ኢትዮጵያ ዓሻራችንን እናኑር፤ አንድ ከሆን ከዚህም በላይ እንችላለን! አዋቂዎች ከ20 በላይ፣ ታዳጊዎች ከ10 በላይ በመትከል ለአገር ያለንን ፍቅር፣ ለትውልድ ያለንን ሥጦታ በተገቢው ስፍራ እንግለጥ ሲሉም መልዕክት  አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም