የሲዳማ ክልል የ6ኛና 8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ውጤት ይፋ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የሲዳማ ክልል የ6ኛና 8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ውጤት ይፋ ተደረገ

ሀዋሳ ፤ነሀሴ 10/2016 (ኢዜአ)፡- የሲዳማ ክልል የስድስተኛና ስምንተኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ውጤት ይፋ ሆነ።
ውጤቱን አስመልክቶ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ በየነ በራሶ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በስድስተኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈታና 48 ሺህ 763 ተማሪዎች ተፈትነዋል።
ከተፈታኝ ተማሪዎች መካከል 75 በመቶዎቹ 50 በመቶና ከዛ በላይ ውጤት በማምጣት ወደ ሰባተኛ ክፍል ማለፍ እንደቻሉ ገልጸዋል።
የስድስተኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ሲሰጥ የመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የተናገሩት የቢሮ ሀላፊው የትምህርት ቤትና ተማሪ ውጤት ለማሻሻል የተሰራው ስራ ውጤት የታየበት ስለመሆኑ አመላካች ነው ብለዋል።
በተመሳሳይ የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ 69 ሺህ 880 ተማሪዎች 54 ነጥብ 1 በመቶ የሚሆኑት ወደ ዘጠነኛ ክፍል የሚያሳልፋቸውን 50 በመቶና ከዛ በላይ ውጤት ማምጣታቸውን ተናግረዋል።
ካለፈው ዓመት አንጻር ከፍተኛ የውጤት መሻሻል የታየበት መሆኑን የተናገሩት አቶ በየነ አምና ከተፈተኑ ተማሪዎች 29 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ማለፍ ችለው እንደነበር አስታውሰዋል ።
በክልሉ ስምንተኛ ክፍል ካስፈተኑ ትምህርት ቤቶች 44ቱ ሙሉ በሙሉ ተማሪዎቻቸውን ማሳለፋቸውን ጠቁመው ምንም ተማሪ ያላሳለፉ ትምህርት ቤቶችም መኖራቸውን አስታውቀዋል ።
በስድስተኛም ሆነ በስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ምንም ተማሪ ያላለፉባቸውና አንድ ተማሪ ብቻ ያሳላፉ ትምህርት ቤቶች ምክንያቱን በመለየት በቀጣይ ውጤት ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሰራ አቶ በየነ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።