ኢትዮጵያ በመጪዎቹ አስር ዓመታት ዋነኛ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ትሆናለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በመጪዎቹ አስር ዓመታት ዋነኛ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ትሆናለች
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በመጪዎቹ አስር ዓመታት ዋነኛ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መዳረሻ እንደምትሆን የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔሃብት ምሁር ፕሮፌሰር ፖል ኮሊየር ገለጹ።
ፕሮፌሰሩ ለፋይናንሻል ታይምስ ድረገጽ በላኩት ጽሁፍ እንዳብራሩት የምእራቡ ዓለም ትኩረቱን ወደ ዩክሬይን እና ጋዛ ባደረገበት ወቅት አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ፊታቸውን ወደ ሩሲያ ቢያዞሩም ጥቂቶች የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የኢኮኖሚ ሪፎርም አድርገዋል ብለዋል።
የፋይናንስ ሥርዓታቸውን ቀደም ብለው ያስተካከሉት ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያና ናይጄሪያ ምጣኔሃብታዊ እንቅስቃሴያቸው በጠንካራ መደላደል ውስጥ በመውደቁ በተወሰነ ደረጃ መረጋጋት ተስኖት እንደነበር ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያና ዛምቢያ የሄዱበት መንገድ ሪፎርሙን ዘላቂ በማድረግ የባለሃብቶችን ቀልብ መሳብ እንደሆነም አንስተዋል።
ፕሮፌሰሩ አክለውም ኢትዮጵያ ላለፉት 30 ዓመታትን በዘለቀው ኢኮኖሚ ስርዓት ምጣኔሃብቷን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ለቻይናውያን ባለሃብቶች ክፍት መደረጉን ገልጸዋል።
ቻይናውያኑም በኢትዮጵያ ያለውን የሰውኃይል እና የምእራባውያኑን ክፍት የገበያ መዳረሻዎች ተጠቅመው ቀላል የማምረቻ ማእከላትን በአዲስ አበባና ዙሪያዋ እንዳስፋፉ አስታውሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በለውጡ ወደ ኃላፊነት መምጣታቸውን ተከትሎ ገበያ መር የምንዛሬ ሥርዓትን ከመተግበር ጀምሮ ምጣኔሃብቱን የተመለከቱ በርካታ ወሳኝ ማሻሻያዎችን በማድረግ ዘላቂ ሃገር በቀል የኢኮኖሚ ሥርዓት ማስተዋወቃቸውን ጠቅሰው፤ኢትዮጵያ አሁን ላይ ግዙፍ ኢኮኖሚ ገንብታለች ብለዋል።
ፕሮፌሰሩ በርካታ የባሕረ ሰላጤው፣ የህንድ፣ የምስራቅ ኤሽያና የተርኪዬ ባለሃብቶች ቀደም ብለው በመግባት ኤኮኖሚውን ወደፊት እያንቀሳቀሱት መሆኑን አስረድተው፤ በዚህም የዓለም ባንክና አይ ኤም ኤፍ አላስፈላጊ የፖሊሲ ቅድ መሁኔታዎችን ሲደረድሩ መቆየታቸውን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የዜጎቹን ህይወት በዘላቂነት ለመቀየር የሚያስችል ጠንካራ ድርድር በማድረግና ሪፎርሙን በመተግበር አስፈላጊ የሚለውን ገንዘብ ማግኘት እንደቻለ ፕሮፌሰሩ አስረድተዋል።
ዛምቢያም በተመሳሳይ በፖለቲካ ሥርዓቷ የሰፈነውን ሙስናን በመቆጣጠር ሪፎርሙን በስኬት መተግበር ከቻለች ትልቅ ለውጥ ማምጣት ትችላለች ማለታቸውን በመረጃው ተመላክቷል።
የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ላይ የሃገሪቱ ተቃዋሚዎች ደስተኛ ባይህኑም ፕሬዝደንት ሃካይንዴ ሂችሌማ ካቢኔያቸውን ብቃት ባላቸው ሰዎች በማዋቀር የኢኮኖሚ ሪፎርም በማድረግ ዛምቢያን ለሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ምሳሌ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም በጽሁፋቸው ገልጸዋል።