የግብርና ምርታማነታቸው የተረጋገጡ ከ1ሺህ 600 በላይ የሠብል ዝርያዎች ለአርሶና አርብቶ አደሩ ተላልፈዋል - የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ምርታማነታቸው የተረጋገጡ ከ1ሺህ 600 በላይ የሠብል ዝርያዎች ለአርሶና አርብቶ አደሩ ተላልፈዋል - የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10/2016(ኢዜአ)፦የግብርና ምርታማነታቸው በጥናትና ምርምር የተረጋገጡ ከ1ሺህ 600 በላይ የሠብል ዝርያዎች ለአርሶና አርብቶ አደሩ እንዲተላለፉ መደረጉን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲቲዩቱ ለግብርና ምርታማነት መዘመን ቴክኖሎጂን በማመንጨት፣ በማስተዋወቅና ትስስር በመፍጠር እየሰራ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፈቶ ኢስሞ (ዶ/ር)፤ ተናግረዋል።
የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የብዕርና የአገዳ ሠብሎችን፣ የቅመማ ቅመም፣ የመድኃኒትና ለሽቶ ቅመማ የሚውሉ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ለአርሶና አርብቶ አደሩ ማስተላለፍ እንደተቻለ ገልጸዋል።
የግብርና ምርታማነት ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መምጣቱ የምርምር ስራው ተጠናክሮ ለመቀጠሉ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከዛሬ 30 ዓመታት በፊት በአንድ ሄክታር የሚገኘው ምርት ከ10 ኩንታል እንደማይበልጥ አስታውሰዋል።
ተጠናክሮ በቀጠለው የግብርና ጥናትና ምርምር አሁን ላይ በአማካይ ከአንድ ሄክታር ከ45 እስከ 50 ኩንታል በቆሎ እንዲሁም እስከ 39 ኩንታል ስንዴ ማምረት መቻሉን አንስተዋል።
በኢንስቲትዩቱ የምርምር ማዕከላት በአንድ ሄክታር እስከ 80 ኩንታል ስንዴ፤ እንዲሁም 120 ኩንታል በቆሎ የማምረት ደረጃ ላይ መደረሱን ጠቅሰው፤ ይህን ለማስፋትም በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ በየዓመቱ ከ30 እስከ 40 ሺህ ለሚደርሱ የግብርና ባለሙያዎች የጥናትና ምርምር ውጤቶችን በስልጠና በማስተዋወቅ ጥቅም ላይ እንዲውሉ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
የግብርና ባለሙያዎች በምርምር የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን ለአርሶና አርብቶ አደሩ በማስፋት ለሰብል ምርታማነት ዕድገት በትብብር መስራት አለባቸው በማለት አሳስበዋል።
በኢንስቲትዩቱ የሠብል ምርምር ዳይሬክተር ፈቃዱ ጉርሙ(ዶ/ር)፤ ተቋሙ ባለፈባቸው ረጅም ዓመታት ለግብርና ምርታማነት ዕድገት አዎንታዊ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ለግብርና ምርታማነት ዕድገት ከፍተኛ ሚና ያላቸውን የሠብል ዝርያዎች በምርምር በማበልጸግ ለገቢና ወጪ ምርት አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።
ለአብነትም ከውጭ የሚገባውን የማኮሮኒ ስንዴና የቢራ ገብስ ምርትን በመተካት፤ በሌላ በኩል እንደ ቦለቄና ሰሊጥ የመሳሰሉ የቅባት ሠብሎችን ምርታማነት በማሳደግ የውጭ ምንዛሬ ግኝቱ እንዲጨምር ማስቻሉን ጠቅሰዋል።
በ150 የሠብል አይነቶች በተደረገ የምርምር ስራም ከ 1 ሺህ 600 በላይ የሠብል ዝርያዎች ምርታማነታቸው ተረጋግጦ ለአርሶና አርብቶ አደሩ መተላለፋቸውን አስታውቀዋል።
የግብርና ምርምር ውጤቶቹ ለአርሶና አርብቶ አደሩ ተላልፈው ከፍተኛ ውጤት እያስገኙ ለመሆናቸው የስንዴና በቆሎ ምርታማነትን በአብነት አንስተዋል።