የፒያሳ አዲስ መልክ፤ የገነትና ልጆቿ አዲስ ሕይወት - ኢዜአ አማርኛ
የፒያሳ አዲስ መልክ፤ የገነትና ልጆቿ አዲስ ሕይወት

አዲስ አበባ ባለፈችበት የከተሜነት ታሪክ ዑደት ውስጥ ፒያሳ የግብይት ማዕከል፣ የአራዶች ሰፈር፣ የከተሜነት ወጎች መቼት ተደርጋ ትቆጠራለች።
ዳሩ ዘመን ገፍቶ፣ አዲስ አበባ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ስበት ማዕከል በሆነች ማግስት ፒያሳ መልክና ልኳ ከዘመን ጋር አልተራመደም።
በዕድሜዋ ልክ ባለመታደሷ፣ በዘመን ርምጃ ገጽታዋን ባለመዋጀቷ ለዕይታም፤ ለኑሮም የማትመች ሰፈር ሆና ቆይታለች።
ፒያሳ ዘመኑን የዋጁ እና ቄንጠኛ የምህንድስና ጥበብ የታከለባቸው ሰማይ ጠቀስ ኪነ-ሕንጻዎች በፈሉባት በዛሬዋ አዲስ አበባ ሠማይ ስር ነትባና ጎስቁላ መታየቷ አልቀረም።
በዚህም ድህነትና መልከ ብዙ ማህበራዊ ጠንቆች የበረከቱባት አካባቢ እንደነበረች ፒያሳን ከልጅነት እስከ ዕውቀት የሚያውቋት ነዋሪዎቿ ዋቢ ናቸው።
ዘመኑን የዋጀችና ነገን ያማከለች አዲስ አበባ ለመገንባት ገቢራዊ በተደረገው የኮሪደር ልማት ከፈረሱ ሰፈሮች አንዷ ስትሆን፤ የፒያሳ ነዋሪዎችም ምትክ መኖሪያ እና ካሳ ተሰጥቷቸው አዲስ ህይወት እየመሩ ይገኛሉ።
ውልደቷም፣ ዕድገቷም፣ ኑሮዋም ፒያሳ የነበረው ገነት ክብረት በኮሪደር ልማት አዲስ መልክ ከያዘችው ፒያሳ ተነስተው ወደሌላ የመኖሪያ መንደር ከተዛወሩ የልማት ተነሺዎች አንዷ ናት።
ገነት ተወልዳ ያደገችባትን፣ ለአቅም ሔዋን ደርሳ ወግ ማዕረግ ያየችባትን፣ ትዳር ይዛ ወልዳ የሳመችባትን፣ በህይወት ውጣውረድም ብዙ የተመለከተችባትን ፒያሳ በብዙ መልኩ ታስታውሳታለች።
ሁለት ወንዶች እና የአንድ ሴት ልጇን ፒያሳ ውስጥ በግል ጥረትና ልፋቷ በችግር ውስጥ ማሳደጓን ትገልጻለች።
ፒያሳ አንድ ምዕተ ዓመት በላይ ባስቆጠሩ ግድግዳቸው የተዛዘለ፣ ጣሪያቸው የነተቡ፣ ጉራንጉርና ስርቻ የነገሰባቸው ቤቶች፣ የነጋገሉ ጠባብ መንገዶች የተሞላች ነበርች።
ገነትም ሶስት ልጆቿን ባሳደገችበት ሁለት በሁለት ሜትር በሆነች ጠባብ ቤቷ የነበራት አኗኗር ምንኛ ፈታኝ እንደነበር ታነሳለች።
በተለይም ቤቷ አስፓልት ዳር በመሆኑ ሰዎች ሰክረው የሚረብሹበት፣ ወንጀለኞች የሚሯሯጡበት፣ ሞገደኛ አሽከርካሪዎች ቤቷን የሚገጩበት እና ሌሎች መልከ ብዙ አስከፊ ትዕይንቶች እንደነበሩ እንዲሁ።
በተለይም በሰፈሩ አልባሌ ዕኩይ ተግባራት የሚፈጽሙ አካላት የሚዘዋሩባት በመሆኑ ልጆቿ እንዳያዩባት ያደረገችው መሳቀቅ ስታወሳ እኔ እና እግዚአብሄር ነኝ የምናውቀው ትላለች።
ገነት ከመሀል ፒያሳ ተነስተው በአየር ጤና አካባቢ በሚገኘው ፋኑኤል በሚሰኘው የጋራ መኖሪያ መንደር ዕጣ ከደረሳቸው ሰዎች አንዷ ስትሆን አዲሱን ቤቷን ከቀድሞዋ ጠባብ ቤቷ ጋር ታነጻጽራለች።
በአዲሱ መኖሪያ መንደሯ የሰላም ዕንቅልፍ መተኛቷ፣ ለልጆቿ አለመሳቀቋ ብቻ ሳይሆን ከቀድሞ ጎረቤቶቿ ጋር በአንድ አካባቢ በመኖሯ መስተጋብሩም አልቀረባትም።
በዚህም ከፒያሳ ጎረቤቶቿ ጋር ዕድርን ጨምሮ የነበራቸው ማህበራዊ ክዋኔዎች በአዲሱ ሰፈርም ቀጥሏል።
በሀዘንም በተድላም ጊዜ መረዳዳት እና የጋርዮሽ የኑሮ ዘይቤያችን ዛሬም አልጎደለብኝም ባይ ናት።
አዲሱ የመኖሪያ መንደር የውሃና የመብራት አገልግሎት የተሟላለት እንደሆነ፤ ልጆቿም ያለምንም መንገላታት የትምህርት ቤት መግባታቸውን ትገልጻለች።
በጋራ መኖሪያ መንደሩ ገና ያልተስተካከለው መንገድ በተለይ በክረምት ወቅት አስቸጋሪ ከመሆኑ በስተቀር ለልጆቿ ሰላምና ምቹ ቦታ በማግኘቷ ክብርት ከንቲባዋን አመሰግናለሁ ትላለች።
በርግጥ የኮሪደር ልማት ያመጣው የአዲስ አበባንና የገነትን የኑሮ መልክ የመለወጥ ዕድል በገነት አንደበት ብቻ ሳይሆን በታዳጊ ልጆቿ በኤልሻዳይ እና አቤም ይገለጻል።
ታዳጊዎቹ ከቤት ወጥቶ እንደ ልጅ መጫወት ብርቅ በሆነበት የፒያሳ ኑሯቸው ወደዛሬው ሰፈራችው መግባታቸው ቦርቆ የማደግ የልጅነት ሕልማችው እንደተሳካ ይቆጥሩታል።
እኔም ወላጆቼም በፒያሳ ኖረናል፤ ለህብረተሰቡ የተሻሻለ ኑሮ ግን የፒያሳን በኮሪደር ልማት መነሳት እደግፋለሁ ስትል ትናገራለች።
ከልጅነት እስከ ዕውቀት በኖረችበት ፒያሳ እና አካባቢው በኮሪደር ልማት የደረሰበትን ደረጃና ገጽታ የኖርኩበት ሰፈር አልመሰለኝም በማለት ትገልጻዋለች።
የኮሪደር ልማቱ በአስቸጋሪ ዕኩይ ተግባራት ውስጥ የነበሩ የፒያሳ ወጣቶችን እንደታደገም ታምናለች።
በዚህም የኮሪደር ልማት ለነዋሪዎች የተሻለ ዕድል ይዞ የመጣ፣ የስራ ዕድል የፈጠረ እና ለከተማ ገጸታም ውበት የሚያላብስ በመሆኑ ለቀጣይ የኮሪደር ልማት ትግበራ ህዝቡ ቅንና ተባባሪ መሆን አለበት ትላለች።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር የስራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ ጥራቱ በየነ ፒያሳና መሰል ነባር የመዲናዋ ሰፈሮች የሀገርን ገጽታ የሚያጎድፉና የህዝብ ክብር የማይመጥኑ ናቸው ነው ያሉት።
የኮሪደር ልማቱ ፕሮጀክት የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችዋን አዲስ አበባ የሀገርና የህዝብ ክብር በምትመጥን ደረጃ ዘመናዊት ከተማ ለማድረግ ገቢራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ፒያሳን ጨምሮ በፕሮጀክቱ ትግበራ የተነሱ በርካታ የመዲናዋ ነዋሪዎች ክብራችውና መብታቸው በጠበቀ አግባብ የተሻለ ሕይወት የሚመሩበት አጋጣሚ እንደተመቻቸላቸው ተናግረዋል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ አምስት ኮሪደር መስመሮች በፍጥነትና ጥራት እየተጠናቀቁ መሆኑን ገልጸው፤ ህብረተሰቡ ለኮሪደር ልማት ትግበራ አስፈላጊውን ትብብር እና ተሳትፎ ማድረጉን አስታውሰዋል።
ቀጣይም ለህዝብ ጥቅም ሲባል ለሚሰሩ የኮሪደር ልማት ስራዎች የተለመደ ትብብሩን እንዲያስቀጥል ጠይቀዋል።