ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባሻገር ጽዱ፣ ውብና ጤናማ አካባቢን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ መሰረት ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10/2016(ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራ  የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባሻገርም ጽዱ፣ ውብና ጤናማ አካባቢን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ መሰረት የሚጥል መሆኑን የአረንጓዴ አሻራ ተሳታፊዎች ገለፁ፡፡

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራና ክህሎት ቢሮ  ከኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፈደሬሽን ጋር በመተባበር የአረንጓዴ አሻራ አካል የሆነው ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሂደዋል ፡፡ 

"የምትተክል ሀገር፤ የሚያፀና ትውልድ" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው ስድስተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተለያዩ ተቋማት ፣ ባለድርሻ አካላትና ግለሰቦች የበኩላቸውን አሻራ እያሳረፉ ነው።

የመዲናዋ ስራና ክህሎት ቢሮ  ከኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፈደሬሽን ጋር በመሆን የዚሁ አካል የሆነውን የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ኪዳነ ምህረት አካባቢ አከናውነዋል ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራና ክህሎት ቢሮ በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አበበ ተቀባ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር እውን የሚሆነው በሁሉም ተሳትፎ ነው ብለዋል ፡፡ 

የአረንጓዴ አሻራ ተግባራት የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባሻገርም ጽዱ፣ ውብና ጤናማ አካባቢን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ መሰረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፈደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ  በበኩላቸው፤ ጎርፍ፣ የአፈር መሸርሸር ፣ የዝናብ መዛባት፣ የአየር ንብረት ለውጥና የደን መመናመንን ለመከላከል መርኃ ግብሩ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከከተማ አስተዳደሩ ስራና ክህሎት ቢሮ ጋር በትብብር የጀመሩትን የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በቀጣይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል ፡፡

የአረንጓዴ አሻራ ለአገር ኢኮኖሚ እድገት የራሱ ዋጋ ያለውና ለገቢ ምንጭነት የሚያገለግል በመሆኑ ሁሉም አሻራውን በማሳረፍ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የመርኃ ግብሩ ተሳታፊ የሆኑት አቶ መንግስቱ ህጉ ችግኝ ለአካባቢ ውበትና ጽዳት ያለውን ሚና በመገንዘብ በየዓመቱ አሻራቸውን እያኖሩ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

ወጣት ኢዩኤል ንጉሱ በበኩሉ ሁሉም ሰው ሊያያትና ሊኖርባት የሚናፍቃትን ውብና አረንጓዴ ሀገር መፍጠር የሚቻለው ዛሬ በሚተከሉ ችግኞች በመሆኑ ሁሉም በዚህ መልካም ተግባር ላይ ሊሳተፍ ይገባል ብሏል፡፡ 

በመርኃ ግብሩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራና ክህሎት ጽህፈት ቤት ስር የሚገኙ ሰራተኞች ፣ የዘጠኝ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ተወካዮች፣ ሰራተኞችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች ተገኝተዋል ፡፡ 

በዘንድሮ  አገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር  7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ግብ መጣሉ ይታወቃል ።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም