በወንጀል ምርመራ ሂደት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ማስከበር የሚያስችል የቴክኖሎጂ ምኅዳር ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በወንጀል ምርመራ ሂደት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ማስከበር የሚያስችል የቴክኖሎጂ ምኅዳር ተፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10/2016(ኢዜአ)፦ በወንጀል ምርመራ ሂደት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ማስከበር የሚያስችል በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራልና የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ዘላለም መንግሥቴ ገለጹ።
ምክትል ኮምሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግሥቴ፤ በኢትዮጵያ ቀደም ሲል የነበረው የሰብዓዊ አያያዝ ችግር ለአገራዊ ለውጡ መወለድ አንዱ ገፊ ምክንያት ነበር ብለዋል።
አገራዊ ለውጡ መወለዱን ተከትሎም የፍትሕና የጸጥታ ተቋማት ላይ ስኬታማ የለውጥ እርምጃ በመውሰድ የተሻለ ተቋማዊ ግንባታ መፍጠር እንደተቻለ ገልፀዋል።
ከአገራዊ ለውጡ በፊት የነበረውን የወንጀል ምርመራ ሂደት በመቀየር ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውንም አስረድተዋል።
በዚህም መንግሥት የሰጠውን ቦታ በማልማት የተጠርጣሪዎችን ሰብዓዊ አያያዝ፣ የምርመራ ቆይታና የጠበቃ ግንኙነቶች፣ ፖሊሳዊ ሥነ-ምግባርንና ሕግና ሥርዓትን ባከበረ መንገድ እንዲከናወን እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
የወንጀል ምርመራ ሂደቱም ዓለም አቀፍ ስታንዳርድን በተከተለ መንገድ በኦዲዮና ቪዲዮ በተደገፈ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተጠርጣሪን ሰብዓዊ መብት ባከበረ መንገድ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ተጠሪጣሪዎች በፈጸሙትና በሚጠየቁት ወንጀል ብቻ መልስ በመስጠት ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮ፣ ከጫናና ኃይል ውጪ በሆነ አኳኋን የወንጀል ምርመራው በጥብቅ ዲሲፕሊን እንዲመራ እየተደረገ መሆኑንም ነው ያስረዱት።
የምርምራ ሂደቱንም የቁጥጥር ማዕከል ባለቤት በማድረግ ተጠርጣሪዎች የሚሰጧቸው የኃሳብ ልውውጦች ፖሊሳዊ ሙያን የተከተለ እንዲሆን ቴክኖሎጂ የአንበሳውን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በፖሊስ የሥራ እንቅስቃሴ የሕግ የበላይነትን በማስከበርና በወንጀል ተግባር የተገኙ አካላትንና ቡድኖችን በሕግ ጥላ ሥር በማዋል ተጠያቂነትን ለማስፈን ቴክኖሎጂ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ብቁ የሰው ኃይል በማደራጀት የፌደራል ፖሊስ በወንጀል መከላከልና በምርመራ ሂደት ውጤታማ የተባሉ የዲጂታል መሣሪያዎችን በመታጠቅ ስኬታማ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በቀጣይም የቴክኖሎጂ አሠራሮችን በማዘመን በክልል የፌደራል ፖሊስ የምርመራ ማዕከላት ጭምር ተደራሽ በማድረግ ለሕግ የበላይነት መከበር አስተማማኝ ሥርዓት ለመዘርጋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።