የመጀመሪያውን የአፍሪካ ከተሞች ፎረም በስኬት ለማስተናገድ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጠናቋል - የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የመጀመሪያውን የአፍሪካ ከተሞች ፎረም በስኬት ለማስተናገድ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጠናቋል - የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10/2016(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የመጀመሪያውን የአፍሪካ ከተሞች ፎረም በስኬት ለማስተናገድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ፎረሙ "ዘላቂ የክትመት ምጣኔ ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ 2063" በሚል መሪ ሀሳብ ከነሐሴ 29 እስከ ጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
አጠቃላይ ዝግጅቱን በተመለከተ የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፋንታ ደጀን በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ፎረሙን በኢትዮጵያ ለማካሄድ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተጠናቀቀ ይገኛል።
በአህጉራዊው የከተሞች ፎረም ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው የአገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና ተወካዮች እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል።
ፎሩሙ አፍሪካዊ ወንድማማችነትን ከማጠናከር በዘለለ አህጉሪቷ ዘመናዊ ከተሞችን ለመገንባት የሚያስችላት ምክክር የሚደረግበት መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያም ፎረሙን በስኬት ለማስተናገድ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የሚመራ ብሔራዊ እና የቴክኒክ ኮሚቴ በማቋቋም የቅደመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
በፎረሙ ከአፍሪካ አገራት በተጨማሪ በሌሎች አህጉር ያሉ ከተሞች እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው ይኸው ፎረም በአድዋ ድል መታሰቢያ አዳራሽ እንደሚከናወን በመጠቆም በመድረኩ የአፍሪካን ቀልብ የሚስብ ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል።
በፎረሙ የአገር መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ ተመራማሪዎች፣ ወጣቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉ ነው ያስታወቁት።
የአፍሪካን አጀንዳ 2063 ላይ መሠረት ያደረጉ የልማት ግቦች፣ ከተሞችን የተመለከቱ የተለያዩ ጉዳዮችና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ላይ ውይይት የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመዋል።
ልዑካኖቹ በመዲናዋ የሚገኙ የተለያዩ መሠረተ-ልማቶችን እንደሚጎበኙም ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከተሞች ያላቸውን ልምድ የሚያካፍሉበት ኤግዚቢሽን መዘጋጀቱን ገልፀዋል።
የአገር መሪዎችና ሚኒስትሮች የሚሳተፉበት የጎንዮሽ ውይይቶች እንደሚካሄዱ የጠቀሱ ሲሆን፤ በተጨማሪም የወጣቶች ሥልጠና በአፍሪካ ልህቀት አመራር አካዳሚ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
ሆቴሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የጸጥታ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ከወዲሁ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ከተሞች ያላቸውን ልምድና ምርጥ ተሞክሮ በመድረኩ እንደሚያካፍሉ አስታውቀዋል፡፡
ሕብረተሰቡ እንግዳ የመቀበል ባህሉን አጉልቶ በሚያሳይ መልኩ በፎረሙ ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን እንዲቀበል ጥሪ አቅርበዋል።
ፎረሙ በየሁለት ዓመቱ የሚቀጥል መሆኑም ተመላክቷል።