ቀጥታ፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የአበባ አትክልትና ፍራፍሬ የወጪ ንግድ ገቢና ተወዳዳሪነትን ያሳድጋል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10/2016(ኢዜአ)፦የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የወጪ ንግድ ገቢና ተወዳዳሪነትን በማሳደግ የዘርፉን እድገት ለማስቀጠል ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር የአበባ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ላኪዎች ተናገሩ።

ኢትዮጵያ በቅርቡ ገቢራዊ ካደረገችው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መካከል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ አንዱ ነው።

ይህም ኢትዮጵያን በገበያ ላይ ወደ ተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት ያስገባት ሲሆን ይህም የውጭ ምንዛሬ በሚያስገኙ ዘርፎች የተሰማሩ ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ታምኖበታል።

ለአብነትም ቡና፣ አበባ፣ ሰሊጥ፣ የቅባት እህሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ሌሎች አገር ውስጥ በማምረት ለውጭ ገበያ ለሚያቀርቡ አካላት ማሻሻያው ትልቅ እርምጃ ነው ተብሏል።

ይህም ብቻ ሳይሆን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተለይም ለአምራች ዘርፉ ከዚህ ቀደም  የሚደረጉ ድጋፎችን በማጠናከር ረገድም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገልጿል። 

ይህም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉ የወጪ ንግድ ገቢና ተወዳዳሪነትን እንደሚያሳድግ ነው የአበባ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ላኪዎች ለኢዜአ የሚናገሩት።

በአበባ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ላኪነት ላለፉት 28 ዓመታት የሰሩት አቶ ጸጋዬ አበበ፤ ዘርፉ ለሥራ ዕድል ፈጠራና የውጭ ምንዛሬ ግኝት እምቅ አቅም እንዳለው ያነሳሉ።

ከዘርፉ የሚፈለገውን ያህል ገቢ እንዳይገኝ አስረውት ከቆዩ ችግሮች መካከል የውጭ ምንዛሬ ላይ የነበረው አሰራር አንዱ መሆኑን አስታውሰዋል።

መንግሥት ተግባራዊ ያደረገው የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚክ ፖሊሲ ይህንን ችግር በመፍታት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግና ተወዳዳሪነትን ለመጨመር ትልቅ መፍትሔ መሆኑን ገልፀዋል። 

ምርትን በጥራትና በብዛት ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ግኝትና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ማሻሻያው ይዞ የመጣውን ዕድል ለመጠቀም ዝግጁ መሆናቸውንም እንዲሁ። 

ማሻሻያው ገቢን በማሳደግና አቅምን በማጠናከር ምርትን በብዛት ለመላክ እንደሚያግዝ የተናገሩት ደግሞ በአበባና አቮካዶ ምርት ወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩት አቶ ነጋ መኳንንት ናቸው።


 

 የኢትዮጵያ አበባ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ላኪዎች ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ዘውዴ በበኩላቸው፤ መንግሥት ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት እየወሰደ ያለውን እርምጃ አድንቀዋል።


 

ተግባራዊ በተደረገው የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያው እንዲወሰን መደረጉ የተላለፈውን ውሳኔ በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ለወጪ ንግድ ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ከውሳኔው በተጨማሪ የወጪ ንግድ ገቢንና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የሚያጋጥሙ ሌሎች ተጓዳኝ ችግሮችን መፍታት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በቀጣይ አራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያን ምጣኔ ኃብት በአማካይ በ8 በመቶ ያህል እንዲሁም የወጪና የገቢ ንግድ ዋጋ ወደ 20 ቢሊየን ዶላር እንደሚያሳድገው ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም