በአማራ ክልል በተናበበና በተቀናጀ መንገድ ተግባራትን በመፈፀም የህዝቡን እርካታ ለማረጋገጥ ይሰራል - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በተናበበና በተቀናጀ መንገድ ተግባራትን በመፈፀም የህዝቡን እርካታ ለማረጋገጥ ይሰራል - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

ባህር ዳር፤ ነሐሴ 10/2016(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በ2017 በጀት ዓመት ተግባራትን በተናበበና በተቀናጀ መንገድ በመፈፀም የህዝቡን እርካታ ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለፁ።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የ2016 በጀት ዓመት የፓርቲና የመንግስት ስራዎች እቅድ አፈጻጸም እና የ2017 እቅድ ኦረንቴሽን መድረክ እየተካሄደ ነው።
ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ አረጋ በመድረኩ ተገኝተው እንደገለጹት፤ በየደረጃው የሚገኙ አመራር አባላት የክልሉን የፖለቲካ፣ ሰላምና ፀጥታ አሁናዊ ሁኔታ በአግባቡ በመረዳት ተልዕኳቸውን መፈጸም ይጠበቅባቸዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከተሰሩ ስራዎች ጎን ለጎን አበረታች የልማት ተግባራት መከናወን መቻላቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በስራ እንቅስቃሴ የታዩ ጠንካራ ጎኖችን በማሳደግና መታረም የሚገባቸውን ድክመቶች በማረም በሁሉም ዘርፍ የተያዙ እቅዶች ተፈፃሚ እንዲሆኑ አመራር አባላቱ ግንባር ቀደም ሚናቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በተቋም ደረጃ ውጤታማ ተግባራትን ከማከናወን ባሻገር በካቢኔ ደረጃ ለሚወሰኑ ውሳኔዎች ጠንካራ አመራር በመስጠት ለውጤት ማብቃት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በየደረጃው የሚገኝ አመራር ነባራዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተቀናጀና በተናበበ አግባብ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባ አብራርተዋል።
የገጠመንን ችግር ለመሻገር የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ስራዎች ላይ ሰርተን በአዲሱ በጀት ዓመት ማሳየት አለብን ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።
ህዝቡን ከገጠመው ችግር ለማውጣት ቁርጠኛ አቋም ተይዞ ስራዎች መከናወን እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ በ2017 በጀት ዓመት የተናበበና የጋራ ስራ በማከናወን የተቀመጡ አቅጣጫዎች የሚፈጸምበት እንደሚሆን ገልጸዋል።
በመድረኩ ከርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽፈት ቤት ሃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላትና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።