የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሃና አርአያስላሴ ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሆናለች፡፡
በፈተናዎች ሁሉ የሚያልፍ ጠንካራና ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ በስኬታማነቷ ተጠቃሽ ሀገር መሆንም ችላለች።
ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሃና አርአያስላሴ፤ በኢትዮጵያ የተፈጠረው ምቹ መሰረተ ልማት በቀጣናው ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ አድርጓታል ብለዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ትግበራው ደግሞ ለኢንቨስትመንት ልማት ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
በ2016 በጀት ዓመት ከ3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ ጥሩ ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰው በቀጣይ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተጨማሪ እድል ይዞ የሚመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እየጨመረ ቢመጣም ኢንቨስተሮች ትርፋቸውን በውጭ ምንዛሬ መውሰድ አለመቻላቸው ለዘርፉ ማነቆ ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም መንግስት ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገት በማስመዝገብ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ተገብቷል ብለዋል፡፡
የፖሊሲ ማሻሻያው የዘርፉ ፈተናዎችን በመፍታት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ፍሰቱን በማሳደግ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡
በዘርፉ የተሰማሩ የኢንቨስተሮችን ጥያቄዎች የሚመልስ፤ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን በዘላቂነት የሚፈታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲውን በተሟላ ሁኔታ መተግበር የሚያስችል ሰላምና ጸጥታ መኖሩን የገለጹት ኮሚሽነሯ፤ ይህም የኢንቨስተሮችን ትኩረት እንድትስብ አድርጓታል ብለዋል፡፡
በመሆኑም የውጭ ባለሀብቶች ያለምንም የጸጥታ ስጋት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡