የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ከዩጋንዳው ቪላ ጋር ነገ ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ከዩጋንዳው ቪላ ጋር ነገ ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 10/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2024/25 የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የመጀመሪያ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ከዩጋንዳው ቪላ ጋር ነገ በካምፓላ ያደርጋል።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ከ45 ሺህ በላይ ተመልካች በሚያስተናግደው ማንዴላ ብሔራዊ ስታዲየም ይካሄዳል።
ኢትዮጵያን ወክሎ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የሚሳተፈው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለጨዋታው ላለፉት ሁለት ሳምንታት በአዳማ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።
ቡድኑ የመጨረሻ የአገር ቤት ልምምዱን ትናንት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ስታዲየም ካደረገ በኋላ ወደ ዩጋንዳ ማምራቱን ኢዜአ ከስፖርት ክለቡ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የሁለቱ ቡድኖች የደርሶ መልስ አሸናፊ በሁለተኛው ዙር ማጣሪያ ከታንዛኒያው ያንግ አፍሪካንስና ከቡሩንዲው ቪታሎ ክለቦች ጨዋታ አሸናፊ ጋር ይገናኛል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 ዓ.ም የውድድር ዓመት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን መሆኑ ይታወቃል።
በ2024/25 የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ከ47 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ 59 ክለቦች ይሳተፋሉ።