በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ አስተማማኝ የወንጀል መከላከልና መቆጣጠር አቅም ተገንብቷል- ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መላኩ ፈንታ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ አስተማማኝ የወንጀል መከላከልና መቆጣጠር አቅም ተገንብቷል- ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መላኩ ፈንታ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ አስተማማኝ የወንጀል መከላከልና መቆጣጠር አቅም መገንባቱን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መላኩ ፈንታ ገለጹ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መላኩ ፈንታ፤ የፌደራል ፖሊስ ያከናወናቸው የሪፎርም ሥራዎች በውጤት የታጀቡ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በፌደራል ፖሊስ ሪፎርም ቅድሚያ ተሰጥቶ ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል ዋነኛው የሰው ኃይልን ማደራጀት እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ተልዕኮውን በአግባቡ መፈጸም የሚያስችል ጠንካራ ኃይል መገንባት መቻሉን አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም ሠራዊቱ በመላው አገሪቱ ተልዕኮውን የሚያስፈጽምበት አደረጃጀቶች በመምሪያ ደረጃ እንዲዋቀሩ መደረጉን አመላክተዋል።
ለአብነትም የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ፣ የተቋማት ጥበቃ፣ የልዩ የፀረ-ሽብር ኮማንዶ ኃይልና ሌሎች ተልዕኮውን ለመወጣት የሚያስችሉ አደረጃጀቶች መፈጠራቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በፌደራል ፖሊስ አስተማማኝ የወንጀል መከላከል አቅም መፍጠሩን ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በምታስተናግዳቸው ዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ እንዲሁም የተለያዩ የአደባባይ በዓላት ያለምንም የፀጥታ ስጋት በሰላም ማከናወን መቻሉን ጠቅሰው፤ ይህ ውጤታማ ስራ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
ከቴክኖሎጂ መስፋፋት ጋር ተያይዞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውስብስብ የወንጀል ተግባራት እንደሚፈጸሙ ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስም ውሰብስብ ወንጀሎችን መሰረት ያደረገ የወንጀል መከላከል ቁመና ገንብቷል ብለዋል፡፡
የወንጀል መከላከሉና የመቆጣጠሩ ሥራ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ጭምር እየተከናወነ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡
ለአብነትም የደኅንነት ካሜራዎች፣ ሕብረተሰቡ በወንጀል መከላከል ሥራ እንዲሳተፍ የሚያደርጉ መተግበሪያዎች እንዲሁም መረጃዎች ወደ አንድ ማዕከል እንዲመጡ የሚያደርግ አሠራር መዘርጋቱን ገልፀዋል፡፡
ይህም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል አቅምን ትርጉም ባለው መልኩ እንዲሻሻል አድርጓል ነው ያሉት፡፡