ቀጥታ፡

ቻይና ለኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች ነጻ የትምህርት እድል ሰጠች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2016(ኢዜአ)፦ ቻይና በተለያዩ ፕሮግራሞች ለሚሳተፉ ለ200 ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች ነጻ የትምህርት እድል ሰጥታለች።

የሽኝት መርኃ ግብሩ በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና የኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስቴር ተወካዮች በተገኙበት በቻይና ኤምባሲ ተከናውኗል።

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ከፍተኛ አማካሪና ምክትል ሃላፊ ሚኒስትር ሺን ኪንሚን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት መንግስታቸው ለኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች በየዓመቱ ሰፊ የትምህርት እድል እየሰጠ ይገኛል።


 

የትምህርት ዕድሉ ተማሪዎቹ አዲስ ልምድ በማካበት ሀገራቸውን በእውቀት እንዲያገለግሉና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ማህበራዊ መስተጋብር እንዲጠናከር የላቀ ፋይዳ እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።

የቻይና መንግስት በየአመቱ 200 ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች በተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞች ዕድል ሲሰጥ የቆየ መሆኑን በማንሳት፣ በዘንድሮ አመትም ተመሳሳይ እድል መሰጠቱን ገልጸዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዓለም አቀፋዊነትና ስኮላርሺፕ ዴስክ ኃላፊ ኢዶሳ ተርፋሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው የቻይና መንግስት በየአመቱ በትምህርት ዘርፍ ለኢትዮጵያ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ኢትዮጵያና ቻይና ያላቸው ሁሉን አቀፍ ግንኙነት በትምህርት ዘርፉም እየተጠናከረ መምጣቱን አስታውቀዋል፡፡

ይህን ተከትሎ የትምህርት ዕድሉ ተማሪዎቹ ሀገራቸውን በእውቀት እንዲያገለግሉ ታላቅ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

የነጻ ትምህርት እድሉ ተጠቃሚ የሆነው ተማሪ ገድፈው ሰውነት ያገኘነው እድል አገራችንን በእውቀት እንድናገለግል የሚያዘጋጀን ነው ሲል ሀሳቡን ገልጿል።

በትምህርት ቆይታችን የምንቀስመውን ዕውቀት የአገራችንን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት እንጠቀምበታለን ሲልም ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም