ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና ልማት በምታደርገው ጥረት አሜሪካ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኝነቷን አሳይታለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና ልማት በምታደርገው ጥረት አሜሪካ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኝነቷን አሳይታለች
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና ልማት በምታደርገው ጥረት አሜሪካ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኝነቷን ማሳየቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ፤ በወቅታዊ የዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት ላይ በማተኮር ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል-አቀባዩ በመግለጫቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ፤ ባለፈው ሳምንት ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የሰዎች ደኅንነት የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ኡዝራ ዘያ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡
ኢትዮጵያና አሜሪካ የጋራ ጉዳዮች በሆኑ የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ፣ ደኅንነትና ልማት ላይ መምከራቸውንም ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሰላም ለማስጠበቅ የምታደርገውን ጥረት፣ የወሰደችውን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያም የሚደነቅ መሆኑ ተነስቷል ብለዋል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና ልማት በምታደርገው ጥረት ለሚገጥሟት ችግሮች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ አሜሪካ ቁርጠኝነቷን አሳይታለች ነው ያሉት፡፡
በሊባኖስ ከ150 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን የሚኖሩ በመሆኑ፤ ችግሮች ተባብሰው የሚቀጥሉ ከሆነ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
ሆኖም በሊባኖስ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የሚያስገድድ አይደለም ብለዋል።
በተጨማሪም የተርኪዬ መንግሥት በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል ያለውን ልዩነት ለመፍታት የድርድር መድረክ በማመቻቸት ላደረገው ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።
የአንካራውን ሁለተኛ ዙር የድርድር መድረክ የመሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ፤ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለው ልዩነት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ኢትዮጵያ ጽኑ ፍላጎት እንዳላት መግለጻቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣዩ የሦስተኛው ዙር ድርድር እንደምትሳተፍ ገልጸው፤ የባህር በር የማግኘት ሕጋዊና ሰላማዊ ጥያቄዋ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በርን በተመለከተ ግጭት እንዲፈጠር አትፈልግም፤ ግጭቶችን ለማስወገድም ጥረት እያደረገች መሆኑን ገልፀዋል።
በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ አስተማማኝ የባሕር በር ለማግኘት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።