ኢትዮጵያ ከኒውዝላንድ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር ትፈልጋለች - አምባሳደር ሃደራ አበራ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከኒውዝላንድ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር ትፈልጋለች - አምባሳደር ሃደራ አበራ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከኒውዝላንድ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደምትፈልግ አምባሳደር ሃደራ አበራ ገለጹ።
ተቀማጭነታቸው በካንቤራ አውስትራሊያ የሆነው አምባሳደር ሃደራ በኒውዝላንድ የኢትዮጵያ ልዩ መልእክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው የተሾሙበትን ደብዳቤ ለኒውዝላንድ ጋቨርነር ጄኔራል ሲንዲ ኪሮ አቅርበዋል።
በተጨማሪም አምባሳደሩ ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተላከ መልዕክትም አደርሰዋል።
ኢትዮጵያ ከኒውዝላንድ ጋር በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም ያላትን ግንኙነት ማጠናከር እንደምትፈልግም አምባሳደሩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ የሆነ የእንስሳት ሀብት ምርታማነቷን ለማሻሻልና ለማሳደግ የኒውዝላንድን ዘመናዊ እውቀት፣ ቴክኖሎጂና ልምድ እንደ ተሞክሮ መውሰድ ትሻለችም ብለዋል።
የኒውዝላንድ ጋቨርነር ጄኔራል ሲንዲ ኪሮ የሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነትና የባለብዙ ወገን ትብብር እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
ኒውዝላንድ በቀጣናዊ መረጋጋትና ዘላቂ ሰላም ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር የምታደርገውን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል
ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ለተላከላቸው መልዕክት ምስጋናቸውን ማቅረባቸውንም ኢዜአ አውስትራሊያ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።