ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በታዳሽ ሃይል ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ናት-የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በታዳሽ ሃይል ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ  መሆኗን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀና አርአያስላሴ ገለፁ።

ለታዳሽ ሃይል ኢነርጂ ፋይናንስና ኢንቨስትመንት አማራጮችን ማፈላለግ ላይ ያተኮረ ውይይት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።


 

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነሯ ሀና አርአያስላሴ በዚሁ ጊዜ ኢትዮጵያ በኢነርጂ ዘርፍ ያላትን አቅም በመጠቀም የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦችን ለማሳካት በትኩረት እየሰራች ነው ብለዋል።

የኢነርጂ ዘርፉ ከዋና ዋና የልማት ግቦች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ዘርፉን ለማልማት የተለያዩ የፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ  ሁሉም የታዳሽ ኢነርጂ አማራጮች ያላትና ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗንም ኮሚሽነሯ ተናግረዋል።

የኢነርጂ ዘርፋ ከፍተኛ ፋይናንስና ኢንቨስትመንት የሚፈልግ በመሆኑ ዘርፉን በሚገባ ጥቅም ላይ ለማዋል ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር እየተሰራ ነዉ ብለዋል።

በኢነርጂ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የተለያዩ ማበረታቻዎች መኖራቸውን የጠቀሱት ኮሚሽነሯ ካለው ፍላጎት አኳያ የግል ዘርፉ ቢሰማራ አዋጭ ኢንቨስትመንት መሆኑን ጠቁመዋል።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ከፍተኛ አማካሪ ጎሳዬ መንግስቴ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ካላት የኢነርጂ አቅም አኳያ ብዙ መስራትና የሃይል ፍላጎትን ማሟላት ይጠበቅባታል ብለዋል።


 

ባለፋት ዓመታት ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት በርካታ ዜጎችን የሃይል ተጠቃሚ ማድረግ ቢቻልም ሁሉንም አካባቢዎች በሃይል ከማስተሳሰርና የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ከማሻሻል አኳያ አሁንም በርካታ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ አብራርተዋል፡፡

አሁን ያለውን የሃይል ተደራሽነት ሽፋን ለማሳደግ መንግስት በዘርፉ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን ነድፎ በአጭር በረጅምና በመካከለኛ ጊዜ  መልማት የሚችሉ የሃይል አማራጮች ላይ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት የንግድና ልማት ጉባኤ የአፍሪካ ተወካይ ዲዓን ሳይንዞጋ በበኩላቸው በአብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት የኢነርጂ ተደራሽነት ውስን መሆኑን ተናግረዋል።


 

በዚህም ዜጎች ከሰልና ጋዝ የመሳሰሉ የሃይል አማራጮችን በመጠቀም የአካባቢ ብክለትና ለጤና እክል እየተዳረጉ መሆኑንም ነው ያነሱት።

የአፍሪካ ህብረት በ2030 አሳካዋለው ብሎ ከያዛቸው የልማት ግቦች አንዱ የኢነርጂ አማራጮችን ማስፋትና የዜጎቸን ህይወት ማሻሻል መሆኑንም አንስተዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጰያ ያላትን የታዳሽ ሃይል ጥቅም ላይ ለማዋል ትላልቅ ኢንቨስትመንቶችና የፋይናንስ ድጋፍ ያስፈልጋታል ብለዋል።

አገሪቷ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይገበር ኢኮኖሚ ለመገንባት የጀመረቻቸው ስራዎች የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ይህንን ስራ በዘላቂነት ውጤታማ ለማድረግ አስተማማኝ ኢንቨስትመንት ማፈላለግ ይገባል ብለዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት ንግድና ልማት ጉባኤ በኢትዮጵያ በታዳሽ ሃይል ልማት ዘርፍ የተለያዩ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑንም ተወካዩ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም