ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የአይ ኤስ ኦ የጥራት ሥራ አመራር ሰርቲፊኬት አገኘ

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 9/2016(ኢዜአ)፡-የአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የአይ ኤስ ኦ  /ISO/ 9001/2015 የጥራት ሥራ አመራር ሰርቲፊኬት አገኘ።

የኮሌጁ ዲን ግሩም ግርማ፤ የጥራት ሥራ አመራር ሰርቲፊኬቱን ከኢትዮጵያ የተስማሚነትና ምዘና ድርጅት በዛሬው ዕለት ተረክበዋል።

ከዚሁ መርሃ-ግብር በኋላ የኮሌጁ ዲን ባደረጉት ንግግር፤ የአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በዘርፉ የላቀ አበርክቶ ያለውና በመዲናዋ በአንጋፋነቱ የሚጠቀስ ተቋም መሆኑን አንስተዋል።

በ82 ዓመታት ቆይታው በቴክኖሎጂና በኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ሙያተኞችን በማሰልጠን ከከተማዋም ባለፈ ለሀገር ልማትና እድገት ባለውለታ መሆኑን ገልፀዋል።

በመሆኑም በዛሬው እለት የአይ ኤስ ኦ  /ISO/ 9001/2015 የጥራት ሥራ አመራር ሰርቲፊኬት ማግኘቱ አገልግሎቱንና ተወዳዳሪነቱን ይበልጥ እንዲያሳድግ የሚያግዝ ነው ብለዋል። 

የኮሌጁን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲሁም የሚያሰለጥናቸውን ባለሙያዎች ይበልጥ ተፈላጊ የሚያደርግ መሆኑንም ተናግረዋል። 

የቴክኖሎጂ ኤክስቴንሽን ተግባራት ጥራታቸውን ጠብቀው የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጡም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተዋል።

የጥራት ሥራ አመራር ሰርቲፊኬቱን ለኮሌጁ ያስረከቡት የኢትዮጵያ የተስማሚነትና ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር መዓዛ አበራ፤ ኮሌጁ ዓለም አቀፍ የጥራት አመራር ሥርዓት መስፈርትን በማሟላቱ ሰርቲፊኬቱ መሰጠቱን ገልፀዋል።

በዚህ የአሠራር ሥርዓት ውስጥ ማለፍ ደግሞ ብክነትን በመቀነስ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመርና ወጥ የሆነ የአሠራር ሥርዓትን ለመከተል ያስችላል ብለዋል።

የአዲስ አበባ የሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አበራ ብሩ(ዶ/ር)፤ ኮሌጁ የአይ ኤስ ኦ የጥራት ሥራ አመራር ሰርቲፊኬት ማግኘቱ የሥልጠና ጥራት ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለዚህ እውቅና በመብቃቱ ለላቀ ሥራ የሚያነሳሳ በመሆኑ ለሌላ ስኬት የጋራ ጥረታችን ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም