ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት ለውጭና ለሀገር ውስጥ ሥራ ስምሪቱ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት ለውጭና ለሀገር ውስጥ ሥራ ስምሪቱ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የማይተካ መሆኑን የስራና ክህሎች ሚኒስቴር አስታወቀ።

ለአገር አቀፍ የግብርና ናሙና ቆጠራ የሰው ኃይል ምልመላ ሂደት መጠናቀቁን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በ2017 በጀት ዓመት ለሚያካሂደው የግብርና ናሙና ቆጠራ የሰው ሃይል ምልመላ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በለማው የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት ለማከናወን የጋራ መግባቢያ ስምምነት ተደርጎ ወደ ሥራ መገባቱ ይታወሳል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚልና የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌን(ዶ/ር) ጨምሮ የሁለቱም ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የምልመላ ሂደቱ ተገምግሟል፡፡

በግምገማው ወቅት የናሙና ቆጠራውን በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ ለማካሄድ የሚያስችል የሰው ኃይል ምልመላ ሂደት አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልቶ መጠናቀቁም ነው የተገለጸው።

አጠቃላይ የቅጥር ሂደቱም በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ የተገለጸ ሲሆን በኢትዮጵያ የስራ ገበያ መረጃ ስርዓት የተደረገው የምልመላ ሂደት ቴክኖሎጂው ለውጭ ሀገር ብቻ ሳይሆን ለአገር ውስጥ ሥራ ስምሪቱ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ወሳኝ መሆኑም ተጠቁሟል።

ከመረጃ ስርዓቱ በርካታ ልምዶች መወሰዳቸውንና የዲጂታል አሰራሩ ከአድሎ የፀዳ፣ ፍትሐዊ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት የተጀመረውን ሀገራዊ ጥረት እንደሚያግዝ ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም