የጋምቤላ ክልል የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ስኬታማ ለማድረግ አመራሩ ህዝቡን አስተባብሮ መሥራት አለበት - አፈ-ጉባዔ ባንቻየሁ ድንገታ - ኢዜአ አማርኛ
የጋምቤላ ክልል የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ስኬታማ ለማድረግ አመራሩ ህዝቡን አስተባብሮ መሥራት አለበት - አፈ-ጉባዔ ባንቻየሁ ድንገታ
ጋምቤላ፤ነሐሴ 09/2016(ኢዜአ)፡-በጋምቤላ ክልል የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ስኬታማ ለማድረግ አመራሩ ህዝቡን አስተባብሮ መሥራት እንደሚጠበቅበት የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታ አሳሰቡ።
የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ የምርጫ ጊዜ 3ኛ የስራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ጉባዔ ሹመቶችን በማጽደቅና ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል።
አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ባንቻየሁ በዚሁ ወቅት እንዳሳሰቡት በክልሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶችን ስኬታማ ለማድረግ በተለይም አመራሩ የወጣቱን ኃይል አስተባብሮ ሊሰራ ይገባል።
አዲሱ የለውጥ አመራር በተለይም በነባሩ አመራር የተጀመሩ ስራዎችን በማስቀጠል የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መላ የክልሉን ህዝብ አስተባብሮ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
እንደ ሀገር ብሎም እንደ ክልል የተጀመረው ለውጥ ፍሬ አፍርቶ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የታየው የአመራር የመተካካት ሂደት እጅግ የሚያኮራና የክልሉን ገጽታ የሚቀይር መሆኑን አፈ- ጉባዔዋ ገልጸዋል።
በተለይም የአመራር መተካካቱ ሂደት የሴቶች የፖለቲካና የውሳኔ ሰጪነት ተሳትፎ በተግባር የተረጋገጠበት ሂደት መሆኑንም አፈ-ጉባዔዋ አስታውቀዋል።
አስቸኳይ ጉባዔው በነበረው የግማሽ ቀን ቆይታው የቀረቡለትን አጀንዳዎችና ሹመቶችን መርምሮ በማጽደቅ ተጠናቋል።