ቀጥታ፡

የሀገርን ኢኮኖሚ ከመደገፍ ባሻገር በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራዊ ሃላፊነታችንን እየተወጣን ነው- በሪሶ አመሎ (ዶ/ር)

ጅማ፣ ነሐሴ 9/2016 (ኢዜአ)፡- የሀገርን ኢኮኖሚ ከመደገፍ ባሻገር በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራዊ  ሃላፊነታችንን እየተወጣን ነው ሲሉ የባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ በጅማ ከተማ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ በሚገመት ወጪ የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባራትን አስጀምሯል።

ዛሬ በተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱም አንድ  የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ ማስቀመጥ፣ የሶስት አቅመ ደካሞች የቤት እድሳት ማስጀመር፣ የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍና የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተካሂዷል።


 

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ  በሪሶ አመሎ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት ተቋሙ የወጪና ገቢ ንግድን ከማሳለጥ ባሻገር የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች ላይም ይሳተፋል።

ለአብነትም በሀገሪቷ በተለያዩ ክፍሎች የትምህርት ቤትና የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ለህብረተሰቡ ጥቅም አውለናል ብለዋል።

ዛሬም በጅማ ከተማ የችግኝ ተከላ እና የደም ልገሳ መርሃ ግብር ማካሄዳቸውን ገልጸው፤ በዚህም ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤትና የአቅመ ደካማ ቤቶችን እድሳት መጀመራቸውንና የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።


 

የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሃግብር በርካታ ወገኖችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ የመደጋገፍ ልምምድ ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባው ነው ብለዋል።


 

የተጀመሩት የበጎ ፍቃድ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተጠናቀው ርክክብ የሚደረግ መሆኑን አንስተው፤ በዋናው ተግባራቸውም በጅማ ከተማ የደረቅ ወደብ ለመገንባት ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ጣሃ ቀመር በበኩላቸው ተቋሙ ለጅማ ከተማ ህብረተሰብ ያደረገው ነገር የሚያስመሰግን ተግባር መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም በጅማ ከተማ ለቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤትና የአቅመ ደካሞች የቤት ግንባታ የተሰጠው ትኩረት የሚደነቅ መሆኑን አንስተው፤ ሌሎች ተቋማትም ይህን መሰል ተግባር መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በጅማ ከተማ ለመገንባት የታሰበው የደረቅ ወደብ ግንባታም ዝግጅቱ ተጠናቆ እንዲጀመር የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ትብብር ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል።

ተቋሙ ላደረገው የክረምት የበጎ ፍቃድ ስራ በተመለከተ አስታያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች በበኩላቸው የሚገነባው ትምህርት ቤት ትውልድን የሚቀርጽ በመሆኑ መሰረታዊ ድጋፍ ነው ብለዋል።

የሰጦ ሰመሮ ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘር ፎዚያ ናስር የህጻናት ትምህርት ቤት የሚገነባ በመሆኑ እንደተደሰቱ ገልጸው፤ "ልጆቻችን እውቀት ሊያገኙ በመሆኑ እናመሰግናለን" ብለዋል።

በአካባቢው የመዋዕለ ህጻናት ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ልጆቻችንን ለማስተማር እንቸገር ነበር ያሉት ነዋሪዋ፤ "ከዚህ በኋላ ለችግራችን መፍትሔ አግኝተናል" ነው ያሉት።

ለሁለት ልጆቻቸው የመማሪያ ደብተርና እስኪርብቶ ድጋፍ ያገኙት  አቶ ገረመው ነጋ በበኩላቸው ይህ ቀላል እገዛ እንዳልሆነና ወገን ለወገን ሲደጋገፍ ከባዱ ችግር እንደሚቃለል ተናግረዋል።

የመረዳዳት እና የመደጋገፍ ባህል የኢትዮጵውያን መገለጫ መሆኑን አንስተው፤ "ለተደረገልን ሁሉ እጅግ አድርገን እናመሰግናለን" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም