ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ላይ ሊቃጡ የሚችሉ ማናቸውንም የጥፋት ሙከራዎች ማክሸፍ የሚያስችል የላቀ አቅም ገንብተናል - የልዩ ኃይልና የጸረ-ሽብር ሰራዊት አባላት

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ላይ ሊቃጡ የሚችሉ ማናቸውንም የጥፋት ሙከራዎች ማክሸፍ የሚያስችል የላቀ አቅምና ዝግጁነት ያላቸው መሆኑን የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የልዩ ኃይልና የጸረ-ሽብር ተመራቂ የሰራዊት አባላት ገለጹ።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በ12ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን የልዩ ኃይልና የጸረ-ሽብር የሠራዊት አባላትን ቢሾፍቱ በሚገኘው የአየር ኃይል ግቢ አስመርቋል። 


 

የልዩ ኃይልና የጸረ-ሽብር የሠራዊት አባላቱ በስልጠናው በቂ ወታደራዊ እውቀት፣ ክህሎትና የመፈፀም ብቃት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ ላይ ሊቃጡ የሚችሉ ማናቸውንም ጥቃቶች፣ ድንበር ዘለል ወንጀሎችንና የሽብር ተግባራትን ማክሸፍ የሚያስችል ብቃትና ዝግጁነት አለን ብለዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል ሻለቃ አብርሃም ተፈራ እና ምክትል አስር አለቃ ሩፋኤል ዘውዱ፤ በቆይታቸው በነፍስ ወከፍ፣ በቡድን፣ በጓድና በመቶ ደረጃ ግዳጅን በላቀ ብቃት መፈፀም የሚያስችል የተግባርና የንድፈ ሃሳብ ስልጠና አግኝተናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ላይ ሊቃጡ የሚችሉ ማናቸውንም የጥፋት ሙከራዎች ማክሸፍ የሚያስችል የላቀ አቅም ገንብተናል ሲሉም ተናግረዋል።

ሌላኛው ተመራቂ አስር አለቃ ይሳቅ ኑረዲን እና አስር አለቃ ባንተ-አምላክ አባተ፤ በስልጠናው ለልዩ ኃይልና ጸረ-ሽብር ስራ ብቁ የሚያደርጉ ፈታኝ መመዘኛዎችን በማለፍ ተመርቀናል ብለዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጡ ማንኛውም የሀገር ውስጥና ድንበር ዘለል የሽብር ወንጀል ለማክሸፍና ማንኛውንም ሀገራዊ ግዳጅ በላቀ ብቃት ለመፈፀም ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።

በኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የልዩ ኃይልና ጸረ-ሽብር ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ምክትል አዛዥ ለስልጠና ሻለቃ ናትናኤል አበራ፤ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ በአስተሳሰብ፣ በባህሪና በችሎታ ብቃት ያላቸውን የሠራዊት አባላት በማፍራት ላይ ይገኛል ብለዋል።

ተመራቂ የልዩ ኃይልና ጸረ-ሽብር አባላትም ከዚህ ቀደም የውጊያ ልምድና ክህሎት ያላቸው፤ በተሰጣቸው ስልጠናም ጠንካራ የአካልና ሥነ-ልቦና አቅም መገንባት እንደቻሉ ገልጸዋል። 

የማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ አዛዥ ተወካይ ሻለቃ ተክላይ አጽብሃ፤ ተመራቂ የሠራዊት አባላቱ በአካል፣ በስልትና ተያያዥ መስኮች መመዘኛ መስፈርቱን አልፈው ብቃታቸውን ያረጋገጡ ናቸው ብለዋል።

በማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ አሰልጣኝ መሰረታዊ ወታደር ሳሙኤል አበራ፤ ለአባላቱ ቀጣይ የሚሰጥን ግዳጅ በላቀ አፈፃጸም መወጣት የሚያስችል የአካልና ሥነ-ልቦና ስልጠና ወስደው ለምርቃት በቅተዋል ብለዋል።

ተመራቂ የልዩ ኃይልና የጸረ-ሽብር የሠራዊት አባላቱ አዳኞቹ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ሲሆን፤ በቆይታቸውም ግዳጅን በብቃት መወጣት የሚያስችል አቅም ማጎልበታቸው ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም