ቀጥታ፡

የጤናማ ትውልድ ግንባታ የሀገር ግንባታ ምሰሶ በመሆኑ የህፃናት አካላዊና የአዕምሮ ጤና ግንባታ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2016 (ኢዜአ)፦ የጤናማ ትውልድ ግንባታ የሀገር ግንባታ ምሰሶ በመሆኑ የህፃናት አካላዊና የአዕምሮ ጤና ግንባታ ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

የኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት፣ ኒውትሬሽን እና የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን የ2016 ዓ.ም አፈጻጸም ሪፖርትና የ2016 ዕቅድ ግምገማ ከፍተኛ የአመራር መድረክ በድሬዳዋ እየተካሄደ ነው።
 
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ መንግሥት የዜጎችን የምግብ ዋስትና እና ስርዓተ ምግብ ለማረጋገጥ ወሳኝ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ወደ ስራ ማስገባቱን ተናግረዋል።
 
በኢትዮጵያ የህፃናት መቀንጨርን በ2022 ዓ.ም ዜሮ ለማድረግ የሰቆጣ ቃል ኪዳን ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ እየተተገበረ ስለመሆኑም አንስተዋል።
 
ባለፉት ሶስት ዓመታት የዜጎችን ምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱንም ገልጸዋል።
 
የስርዓተ ምግብና ኒውትሬሽን ትግበራን ለማሳካት በክልሎች ተቋማዊ አደረጃጀት መፈጠሩ ትልቅ እርምጃ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
 
ከፅንስ እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የተስተካከለ ስርዓተ ምግብ ማረጋገጥ መቀንጨርን ማስቀረት የሚቻል መሆኑን ጠቅሰው በሁሉም መስክ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ለህፃናት የተሟላ ዕድገት ትኩረት መስጠት ይገባል ብለዋል።
 
የጤናማ ትውልድ ግንባታ የሀገር ግንባታ ምሰሶ በመሆኑ ለህፃናት አካላዊና አዕምሯዊ ጤና የምግብና ኒውትሬሽን ስርዓትን ማረጋገጥ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
 
የፌደራል መንግሥት የመቀንጨር ችግርን ለመቅረፍ ሀገር በቀል የሆነውን የሰቆጣ ቃልኪዳን በመተግበር ውጤት እያስመዘገበ ስለመሆኑም አንስተዋል። 
 
መንግስት አስፈላጊውን በጀት እየመደበ በመሆኑ ክልሎችም ለሀገርና ለትውልድ ጥቅም የሚሰራውን ንቅናቄ ውጤታማ ለማድረግ የአቻ በጀት ምደባን እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል። 
 
የሰቆጣ ቃል ኪዳን ከሀገር አልፎ ለሌሎች ሀገራትም ጥሩ ተሞክሮ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም ተግበራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
 
እንደ አጠቃላይ በጤናው ዘርፍ ፍትሐዊና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለማረጋገጥ የማህበራዊ ጤና መድን ስርዓት እየተተገበረ እንደሆነ አንስተዋል።
 
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ፤ በአሁኑ ወቅት 39 በመቶ ከአምስት ዓመት በታች ህፃናት የመቀንጨርና 11 በመቶዎቹ የመቀጨጭ ሰለባ ናቸው ብለዋል።



 
በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የማህበረሰቡን የአመጋገብ ባህል ማሳደግ፣ የምግብና ስርዓተ ምግብ ደህንነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
 
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፤ የግብርና ምርትን በዓይነት፣ በብዛትና በጥራት በማምረት ስርዓተ ምግብን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።



 
የሌማት ትሩፋትና የአረንጓዴ አሻራ ከስርዓተ ምግብ ተኮር ግብርና ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ስለመሆኑም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም